አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17/ 2017 ዓ/ም፦ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በሀገሪቱ አንዳንብ አካባቢዎች “የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳትና የዜጎች መፈናቀል” እያስከተሉ ያሉ ግጭቶች ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉም አካላት “ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ” ሰላማዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን እንዲከተሉ በሚወክላቸው በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰራተኞች ስም ጠየቀ።
ኮንፌዴሬሽኑ ታኅሳስ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ያካሄደውን 20ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተከትሎ ለጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ በጻፈው ደብዳቤ ሠራተኞች እየደረሰባቸው ያለውን የኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን በአጽንዖት ገልጿል።
ኢሠማኮ በጉባኤው በሃገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች እየተካሄዱ የሚገኙ ግጭቶች ያስከተሉት የኢኮኖሚ መናጋት፣ የኑሮ ውድነት ቀውስ ማስከተሉን ጠቅሶ ይህም ዝቅተኛ ተከፋይ የሆኑ ሰራተኞችንና ቤተሰቦቻቸውን መቋቋም ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ማድረሱን በደብዳቤው ገልጿል።
ከዚህ በፊት የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም የገቢ ግብር እንዲቀንስ እና ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን ለጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ በተደጋጋሚ መጠየቁን የጠቀሰው ኮንፌዴሬሸኑ ሆኖም የተሰጠ አንዳች ምላሽ አለመኖሩ እንዳሳዘነው ጠቁሟል።
ይህን ተከትሎ “ሠራተኛው በአሁኑ ሰዓት የመኖር እና ያለመኖር ጥያቄ ውስጥ ገብቷል” ያለው ኮንፌዴሬሸኑ ከደመወዝና ከተለያዩ አበሎች የሚቆረጠው የሥራ ግብር እንዲቀንስ ባወጣው የአቋም መግለጫ ጠይቋል።
እንዲሁም በሃገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች በመካሄድ ላይ ያሉት ግጭቶች ከሚያደርሱት ሰብአዊ ጉዳት በተጨማሪ በሃገር ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ተጽዕኖ እያሳደሩ በመሆኑ ሁሉም ወገኖች ሰላማዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን እንዲከተሉ አሳስቧል።
ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን በተመለከተ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ 1156 በተደነገገው መሰረት ከሶስትዮሽ አካላት የተውጣጣ አባላት ያሉት ዝቅተኛ የደመወዝ ቦርድ ተቋቁሞ ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቋል።
በተጨማሪም በሃገሪቱ የሚገኙ ሰራተኞች ለተለያዩ የልማት ስራዎች ግንባር ቀደም አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁሞ “ይህ ልማቱን እያስቀደመ ከዕለት ጉርሱ እየቀነሰ የሚያወጣውን ሰራተኛ እንደማንኛውም የሃገሪቱ ዜጋ ጥያቄው ሊመለስና ሊደመጥ ይገባል” ሲል አበክሯል።
በመሆኑም የኮንፌዴሬሸኑን ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ጠርተው እንዲያነጋግሩ ኢሠማኮ ለጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ በጻፈው ደብዳቤ ጥሪ አቅርቧል።
ኢሠማኮ መንግስት ቋሚ ገቢ ላላቸው ሰራተኞች የገቢ ግብር እንዲቀንስ እና እየጨመረ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ ተጨማሪ እርምጃዎችን እንዲተገብር ሲጠይቅ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ኮንፌዴሬሽኑ በህዳር ወር 2017 ዓ.ም ሰራተኞች የሚያጋጥሟቸውን የፋይናንስ ተግዳሮቶች ለመቅረፍ አስቸኳይ የኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነት እንዲደረግ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ማስገባቱ ይታወሳል።
በዚህም ለሰራተኛው ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰንና የገቢ ግብር እንዲቀንስ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቆይቷል። አስ