ቢዝነስዜና

ዜና፡ ግዙፉ የቻይና ኤሌክትሪክ መኪና አምራች ቢዋይዲ በኢትዮጵያ በአምስት የኤሌክትሪክ ሞዴሎችን ለሽያጭ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16/ 2017 ዓ/ም፦ የቻይናው የመኪና አምራች ቢዋይዲ (BYD) አምስት የኤሌክትሪክ ሞዴሎችን  በማቅረብ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ በይፋ መግባቱን አከፋፋዩ ሞኤንኮ አስታውቋል።

በኤሌክትሪክ ተስከርካሪ አምራችነት ዘርፍ ታዋቂ የሆነው ኩባንያው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ትላልቅ የመኪና አከፋፋዮች አንዱ ከሆነው ሞኤንኮ ጋር በመተባበር ወደ ገበያ መግባቱን በአዲስ አበባ በተካሄደው የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ አስታውቋል።

በተጨማሪም ቢዋይዲ ለደንበኞቹ የመኪና ሽያጭ እና የጥገና አገልግሎቶችን ለማቅረብ በአዲስ አበባ ቃሊቲ ማሳያ ክፍልና የድህረ ሽያጭ አገልግሎት ማዕከል ከፍቷል።

“ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ ገበያ መግባቱ ለቢዋይዲ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና መስፋፋት ትልቅ ምዕራፍ ነው” ሲሉ የቢዋይዲ አፍሪካ የሽያጭ ዳይሬክተር ራሚ ያኦ ገልጸዋል። 

የለንደኑ ኢንችኬፕ ኩባንያ የሆነው ሞኤንኮ በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያ ባጋራው ጽሁፍ፤ የቢዋይዲ መኪኖችን በአዲስ አበባ መገናኛ አካባቢ ባለው ቃል ህንፃ ላይ አዲስ የተሽከርካሪ ማሳያ ክፍል በይፋ መክፈቱን አስታውቋል። 

በኢትዮጵያ የቢዋይዲ ህጋዊ አከፋፋይ የሆነው ሞኤንኮ ውበት እና ጥንካሬ ያላቸው የተለያዩ የኤሌክትሪክ እና የሀይብሪድ አማራጭ መኪኖችን ከ6 አመት ወይም እስከ 150,000 ኪ.ሜ የሚደርስ የተሸከርካሪ ዋስትና እና ከ8 አመት የባትሪ ዋስትና ጋር ለሽያጭ ማቅረቡን ገልጿል።

እንደ ቢዋይዲ ገልጻ ኩባንያው በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ 13 አገራት እና ክልሎች ውስጥ ይገኛል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ግዙፉ የቻይና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኩባንያው በፈረንጆቹ አቆጣጣር በ2024 የመጀመሪያዎቹ አስራ አንድ ወራት ውስጥ 3.76 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎችን ለገዢዎች ያቀረበ ሲሆን  በህዳር ወር ብቻ 506,804 ሽያጭ ማከናወኑን ሮይተርስ በቅርቡ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ በመጪው 10 ዓመታት ከ432 ሺህ እስከ 500 ሺህ የሚሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችል እቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር በህዳር ወር አስታውቋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች 95 በመቶ የሚሆኑት የኤሌክትሪክ እንደሚሆኑ ገልጿል።

በአሁኑ ወቅትም ከውጭ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው የሚገቡ የኤሌክትሪክ መኪኖች ቀረጥ 5 በመቶ ብቻ ሲሆን በከፊል ተገጣጥመው የሚገቡት ደግሞ ምንም አይነት ቀረጥ እንደማይከፈልባቸው አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ 15 የሚጠጉ የግሉ ዘርፍ ባለሃብቶች የኤሌክትሪክ መኪኖችን በመገጣጠም ለአገልግሎት እያቀረቡ መሆኑን ተገልጿል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button