ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና: "በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በአልሚ ምግብና በመድሀኒት አቅርቦት ችግር ምክንያት ዜጎች ለጉዳት ተዳርገዋል" - ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16/2017 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት የደረሰው በአልሚ ምግብና በመድሀኒት አቅርቦት ችግር ምክንያት ነው ሲል የክልሉ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።

በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሳቢያ 110 ሺህ ወገኖች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ቡግና ላይ የተከሰተውን በተመለከተ የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሠርካዲስ አታሌ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኮሚሽኑ በኩል የሚደረገው የምግብ ድጋፍ በተገቢው መንገድ ሲተላለፍ ቆይቷል ብለዋል፡፡

ነገር ግን መደበኛ ምግብ ማቅረብ ብቻውን ለነዚህ አካባቢዎች በቂ አይደለም ሲሉ የጠቆሙት ምክትል ኮሚሽነሯ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዳ አከባቢ በመሆኑ የአልሚ ምግብ አቅርቦት የሚፈልጉ አካባቢዎች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

“በኛ በኩል የምግብ እህል በተገቢው ጊዜና ሁኔታ የቀረበ ቢሆንም በአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት USAID በኩል የሚተላለፉ የደጋፊ ምግቦችን /Supplements/ በወቅቱ ባለማድረስ በመጣ ክፍተት ችግሩ ተከስቷል” ሲሉ ማስታወቃቸውን ከክልሉ ኮሚሽን ማስተባበሪያ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ደረጃ ከፍተኛ SAM (Severe Acute Malnutrition) እና መካከለኛ MAM (Moderate Acute Malnutrition) በሚል በህክምና ባለሙያዎች ከተለየ በኋላ የአልሚ ምግብ ለተጎጂዎች መቅረብ ነበረበት ሲሉ አውስተዋል፡፡

ይሄንን ድጋፍ ለማድረስ አካባቢው በጸጥታ ችግር ውስጥ ስለነበር ማድረስ አልተቻለም ያሉት ሃላፊዋ በአንዳንድ ቦታዎች ዝርፊያም ተፈጽሟል፣ ዜጎች በነዚህ ምክንያቶች ለችግር ተዳርገዋል ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና አካባቢ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት አልሚ ምግብ ማድረስ ባለመቻሉ ዜጎች ላይ ተጨማሪ ጫና ፈጥሯል ሲል ገልጸዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች በጣም ከፍተኛ የርሀብ ጊዜ ብለን በምንገልጻቸው በ2016 ሀምሌ፣ ነሀሴና በ2017 መስከረም ወራት 100% በ JOEP የምግብ እህል ድጋፍ በአመልድ በኩል ሲተላለፍ ቆይቷል ብለዋል።

በዚህ መሰረት ለቡግና ወረዳ ለ110 ሺ ተጎጂዎች 4 ሺ 146 ኩንታል ስንዴ እና 414 ኩንታል አልሚ ምግብ ከፌደራል አደጋ ስጋት ተፈቅዶ በመጓጓዝ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የአሜሪካን ድምጽ ሬድዮ በታህሳስ 16 ቀን 2017 ዓ.ም ዘገባው በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በ16 ቀበሌዎች በተከሰተው የምግብ እጥረት የተጎዱ ሕፃናትንና እናቶች ለመታደግ የተሰራጨው የአልሚ ምግብ ርዳታ በቂ እንዳልኾነ፣ ወላጆች፣ የቡግና ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊና ሐኪሞች እንደነገሩት አስደምጧል።

መንግስት ሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል በቂ ክምችት አለኝ፣ የተሟላ ዝግጅት አድርጊያለሁ ሲል መግለጹን ትላንት ታህሳስ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ሰብዓዊ እርዳታ የሚሹ ወገኖችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል አሁናዊ በቂ የሰብዓዊ ድጋፍ ክምችትና ዝግጅት አለ ማለታቸው በዘገባው ተካቷል።

በተጨማሪም በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በህጻናት መቀንጨርና በምግብ እጥረት ለተጎዱ ከ110 ሺህ በላይ ሰዎች ከሁለት ወራት በኋላ የርዳታ እህል መጓጓዝ መጀመሩን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት መግለጹን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችንም ይታወሳል።

እርዳታው መጓጓዝ የጀመረው በጸጥታ ችግር ምክንያት ላለፉት ሁለት ወራት እርዳታ መድረስ ባለመቻሉ በሀገር ሽማግሌዎች ስምምነት መደረጉን ተከትሎ መሆኑን በዘገባው ተመላክቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button