ዜናፖለቲካ

ዜና፡ መንግስት ኢሰመጉ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን አገደ፤ የታገዱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ቁጥር አራት ደረሷል 

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17/ 2017 ዓ/ም፦ የሲቪል ማህበረስብ ድርጅቶች ባለስልጣን፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን (EHRDC) “ገለልተኛ ባለመሆን ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ ተንቀሳቅሰዋል” በሚል  ምክንያት ማገዱ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC) ከባለሥልጣኑ ታኅሳስ 16 ቀን 2017 ዓ.ም በተላከለት ደብዳቤ መታገዱን ዛሬ ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ አረጋግጧል።

ማዕከሉ ለመታገድ የተሰጠው ምክንያት ” ባለስልጣኑ ድርጅቱ ከተቋቋመበት አላማ ውጭ መንቀሳቀስ፣ ገለልተኛ አለመሆንና ግልጽ የሆነ የአደረጃጀት መዋቅር የሌለው መሆኑን በተደረገ ክትትል እና ግምገማ ተረጋግጧል” የሚል መሆኑን አስታውቋል።

ድርጅቱ በባለስልጣኑ አደረኩት ባለው ምርመራ ስለመከናወኑ እንደማያውቅ እና በእግድ ደብዳቤው የተጠቀሱት ውንጀላዎች ማዕከሉን የማይመለከቱ እንደሆኑ በመግለጫ ገልጿል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በዛሬው ዕለት ባወጣው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫም ስራዎቹን “በፍጹም ገለልተኝነት”፣ “ኃላፊነት በተሞላበት ጥንቃቄ” እና “የድርጅቱን መርሆዎች በተከተለ መልኩ ብቻ ሲያከናወን” መቆየቱን ገልጿል።

በተጨማሪም ድርጅቱ ግልፅ የአደረጃጀት መዋቅር ኖሮት ለአመታት በርካታ ስራዎችን እየሰራ ያለ መሆኑ እየታወቀ ከባለሥልጣኑ “ግልጽ የሆነ የአደረጃጀት መዋቅር የሌለው” በሚል የተሰጠው አስተያየት “ግልጽ ባለመሆኑ ለባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ባቀረብነው የማብራሪያ መጠየቂያ ደብዳቤ ላይ መግለጻችንን ለማሳወቅ እንወዳለን” ብሏል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን መታገዱንም የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ኢሰመጉን “ከተቋቋመለት ዓላማ ውጭ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ያደርጋል” በሚል ባለሥልጣኑ መታገዱን ገለጿል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጀቱ በተደጋጋሚ ከመንግስት አካላት በሚደርስበት ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች ምክንያት ስራውን በአግባቡ ለመስራት መቸገሩን ማስታወቁ ይታወሳል።

የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ማስፈራሪያና ዛቻ እንደሚፈጸሙበት የገለጸው ድርጅቱ ዋና ዳይሬክተሩ ዳን ይርጋ በዚኹ ዛቻና ማስፈራሪያ ሳቢያ ከአገር ለመሰደድ እንደተገደዱ መግለጡ ይታወቃል። 

በቅርቡ የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከልን (ካርድ) እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች የተሰኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በድጋሚ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣኑ መታገዳቸው ይታወቃል።

በዚህም አጠቃልይ በመንግስት የታገዱ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አራት ደርሰዋል።

ካርድ በድጋሚ ለመታገድ ያደረሰው ምክንያት ቀደም ሲል ተጥሎ የነበረው እገዳ ሲነሳ “የተገለጸለትን የእርምት እርምጃዎች ባለመውሰድ“ እንዲሁም “ለተሰጠው ማስጠንቀቂያ ትኩረት መንፈግ/አለመስጠት” በሚል መሆኑን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል።

በተመሳሳይ መልኩ ባለስልጣኑ ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ (AHRE) ላይ ጥሎ የነበረውን አግድ ማንሳቱ ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button