ማህበራዊ ጉዳይዜናፖለቲካ

ዜና: በአስገዳጅ የሚሊሻ ስልጠና ሳቢያ በሰንዳፋ ከተማ ጠዋት ላይ የባጃጅ እና የፈረሰ ጋሪ እቅሰቃሴ መገደቡ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21/2017 ዓ.ም፡- በኦሮምያ ክልል ሰንዳፋ ከተማ የባጃጅ ሹፌሮች እና የፈረስ ጋሪ አስጋሪዎች በአስገዳጅ ሁኔታ የሚሊሻ ስለጠና እንዲወስዱ በመደረጉ የባጃጅ እና የፈረስ ጋሪ እንቅስቃሴ መገደቡ ተገለጸ፤ የከተማዋ ነዋሪዎች በትራንስፖረት እጥረት ችግር ላይ መውደቃቸውን አስታውቀዋል።

በግዳጅ እንዲወስዱ እየተደረገ ያለው የሚሊሻ ስልጠናው የተጀመረው ባሳለፍነው ሳምንት አርብ ታህሳስ 18 ቀን 2017 ዓ.ም መሆኑን እና እስከ ጥር ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቀጥል ለአዲስ ስታንዳርድ የገለጹልን የከተማዋ ነዋሪ በስልጠናው ሳቢያ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ተኩል እስከ 3 ሰዓት ተኩል ትራንስፖርት እንዲገደብ ማድረጉን አስታውቀዋል።

በአስገዳጁ ስልጠና ሳቢያ ብዙ ገቢ ማጣቱን ለአዲስ ስታንዳርድ ያስታወቀው የባጃ ሹፌር ሌሊሳ ማሩ (ለደህነቷ ሲባል ስሙ የተቀየረ) “ሒወቴን የምመራው ተማሪዎችን ከትምህርት ቤት በማመላለስ ነው፤ 14 የሚሆኑ በኩንትራት ወደ ትምህርት ቤት የማመላልሳቸው ተማሪዎች አሉኝ፤ በሚሊሻ ስልጠናው ምክንያት የገባሁትን ውል መፈጸም አልቻልኩም፣ የገባሁትን የኩንትራት ውል ባለመፈጸሜ  በድጋሚ ዕድሉን ላላገኝ  እችላለሁ የሚል ስጋት አድሮብኛል” ሲል ገልጿል።

ሌሊሳ በተጨማሪም ስልጠናው እየተሰጠ የሚገኘው “በሰንዳፋ የፀሐይ ሃይል ቴክኖሎጂ እቃዎች ማምረቻ ፋብሪካ” ግቢ ውስጥ መሆኑን አስታውቋል።

የሚልሻ ስልጠናውን መውሰድ ወደ ስራ ለመመለስ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን ጠቁሟል፤ ስልጠናውን ያልወሰዱ የባጃጅ ሹፌሮች ፍቃድ እንደማያገኙ እንደተነገራቸው አስታውቋል።

ስልጠናውን እንዲወስዱ የተገደዱበትን ምክንያትም ለጸጥታ ችግር የሚል ብቻ መሆኑን አመላክቷል፤ ሌላ የተገለጸላቸው ምክንያት አለመኖሩን ገልጿል።

ሌላኛ ስሙ ለደህንነቱ ሲል እንዲገለጽ ያልፈለገ ሹፌር በበኩሉ “ ስለጠናውን ካልወሰድኩ ፍቃድ ስለማይታደስልኝ እና ቤተሰቤን ማገዝ ስለማልችል፣ ስልጠናውን ከመውሰድ ያለፍ ሌላ ምንም ዕድል የለኝም” ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል። የከተማዋ ባለስለጣናት ስልጠናውን መውሰድ አስገዳጅ የሆነበት ምክንያት ለጸጥታ ችግር ሲባለ ነው የሚል ምክንያት ብቻ እንደነገሯቸውም አስታውቋል። “ምንም አይነት ዝርዝር ምክንያት አልነገሩንም” ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው የተጣለው ገደብ በትራንስፖርትላይ የሚፈጥረው ችግር እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል። የከተማዋ ነዋሪ የሆነች አንዲት እናት የእንቅስቃሴ ገደቡ በዕለይ እንቅስቃሴዋ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጻለች፤ “ሶስት እና አራት ኪሎሜትር ለሚርቀው የተማሪ ልጄ ትምህርት ቤት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የምጠቀመው ባጃጅ ነው፣ አሁን ግን በየዕለቱ የ11 አመት ልጄን ትምህርት ቤት ለማድረስ በእግሬ መጓዝ ይጠበቅብኛል፣ ከዚያም ስራየ አዲስ አበባ በመሆኑ ወደ አዲስ አበባ ትራንስፖርት ይዤ እሄዳለሁ” ስትል ተጽእኖውን አጋርታናለች።

በተመሳሳይም የመንግሥት ሠራተኛ መሆኑን የገለጸልን የከተማዋ ነዋሪ የዕለት ተዕለት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል ሳይደረግ ይሄ እርምጃ በመወሰዱ ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረበት ገልጾልናል።

“የዘጠኝ አመት ልጄን ትምህርት ቤት እንዲያደርስልኝ ኩንትራት የከፈልኩት ሹፌር በስልጠናው ሳቢያ ስራ በመከልከሉ እራሴ ማድረስ ይኖርብኛል፤ ኩንትራት የከፈልኩት የባጃጅ ሹፌር ልጄን ጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ መጥቼ ወደ ትምህርት ቤት ልውሰደው የሚል አማራጭ ያቀረበልኝ ቢሆንም ሰዓቱ በጣም ሌሊት ስለሚሆን ፍቃደኛ አልሆንኩም፣ ባለቤቴ በቅርቡ ልጅ በመውለዷ የሌላ ቤተሰብ እገዛ ማግኘት አልቻልኩም” ሲል ነግሮናል።

በከተማዋ የፈረስ ጋሪ የሚያሽከረክሩም ስልጠናውን በግዳጅ እንዲወስዱ ተደርገዋል፤ “ስልጠናውነ ካላጠናቅን እና የምስክር ወረቀት ካልያዝን መስራት እንደማንችል ተነግሮናል” ሲል የገለጸልን የፈረስ ጋሪ አሽከርካሪ “ስልጠናው ጠዋት 12 ሰአት እንደሚጀምር እና እስከ አራት ሰዓት እንደሚቆይ” አስታውቋል።

“ህይወት እጅግ ፈታኝ ሁኗል፣ ነገር ግን አማራኝ የለኝም” ሲል ተናግሯል።

የአከባቢው ባለስልጣናት ስልጠናውን እንዲወስዱ እየተደረገ ያለው ምክንያት ለጸጥታ ሲባል ነው እንዳሏቸው ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቋል። “ስልጠናውን ካጠናቀቅን በኋላ በምሽት እና አስፈላጊ በሆነ ሰአት የከተማዋን ጸጥታ በማስጠበቅ ስራ ላይ እንደምንሰማራ ተነግሮናል” ብሏል።

በኦሮምያ ክልል አስገዳጅ ስልጠና ሲሰጥ ይህ የመጀመሪያ አይደለም፤ ከዚህ በፊት አዲስ ስታንዳርድ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አርሶ አደሮች በግዳጅ ለውትድርና እንዲሰለፉ ምክንያት የሆነውን “ጋቸና ሲርና” የተሰኘውን የክልል ሚሊሻ ምልመላ ሥርዓት ትግበራን መዘገቡ ይታወሳል።

በዚህ ትግበራ መሠረት አርሶ አደሮች የግብርና ቁሳቁስ ለማግኘት የሚሊሺያ ስልጠና መውሰድ ይጠበቅባቸው የነበረ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በምልመላ ወቅት ለዕስር እንደሚዳረጉ ተገልጿል።

በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ለወታደራዊ ስልጠና በግዳጅ የሚወሰዱ ወጣቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ ዘገባ አቅርበናል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button