![](wp-content/uploads/2025/02/IMF-6-1-1024x632-1.jpg)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 3/2017 ዓ.ም፡- የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ፣ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተግዳሮቶች የተሞላ መሆኑን አስታውቀው፣ የኢኮኖሚ ማሻያው “ፈታኝ” ሲሉ በመግለጽ “ጊዜ የሚወስድ” መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአለም አቀዱ የገንዘብ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት የካቲት 1 እና 2 ቀናት 2017 ዓ.ም ጉብኝት አካሂደዋል፤ በጉብኝታቸውም ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መክረዋል።
ከኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ጋር በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ዳይሬክተሮ በኢትዮጵያ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ጉብኝት ያካሄዱት ዳይሬክተሯ ህብረተሰቡ እነዚህን ፖሊሲዎች ተግባራዊ ለማድረግ “አንድነቱን እንዲጠብቅ” ሲሉ አሳስበዋል፣ ማሻሻያው በመጨረሻም “አስደናቂ ውጤት” እንደሚያመጣ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ከባድ ነው” ሲሉ የገለጹት ዳይሬክተሯ ሃላፊዋ ጆርጂዬቫ “ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም እጅግ መልካም ውጤተሮች ይዞ ይመጣል” ሲሉ ተናግረዋል።
የማሻሻያ እርምጃዎቹ መካከል “አንዳንዶች ቀድሞውኑ ግልጽ እየሆኑ ነው” ያሉት ዳይሬክተሯ “ህብረተሰቡም በኢኮኖሚ ማሻሻያው ላይ አንድ በመሆን ሊደግፍ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።
ባለፈው አመት 2024 ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው የ8 ነጥብ አንድ በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ተቋማቸው ተንብዮት ከነበረው የስድስት ነጥብ አንድ በመቶ እድገት ብልጫ ያለው መሆኑን በመጥቀስ “ኢትዮጵያ የምትኮራበት ብዙ ነገር አለ” ሲሉ አስታውቀዋል።
የኢኮኖሚ መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያ ለቀጣይ የኢኮኖሚ እድገትና መረጋጋት ያላትን ቁርጠኝነት በማሳየት ለሌሎች የአህጉሪቱ ሀገራት ተምሳሌት እንድትሆን ያደርጋታል ብለዋል።
በተለይም የፊስካል ፖሊሲዉን በማሳደግ፣ የኢኮኖሚዉን መዋቅራዊ ችግሮችን በመፍታት እና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት የዜጎችን የኑሮ ደረጃን የሚያሻሻሽል መሆኑን ተናግረዋል።
ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ኢትዮጵያ የነደፈችዉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ላይ ለዉጥ ከማምጣቱ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማስመዝገብ ለሚጥሩ የአፍሪካ ሀገራት መሪ ማዕቀፍ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ለኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራማችን የሚያደርገውን የቀጠለ የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፍ የእርስዎንም የግል ጥረት እና አስተዋፅዖ ከፍ ያለ ዋጋ እንሰጠዋለን ሲሉ ገልጸዋል።
በአይኤምኤፍ የገንዘብ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ታላላቅ የድጋፍ መርሃ ግብሮች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም በሀገር በቀል ርዕይ እና የለውጥ አጀንዳ ላይ የተመሠረተ የእድገት እና የልማት ህልሞቻችንን በሚገባ ቀርፆ የያዘ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ገቢን ለማሳደግ በሚል እያከናወነች ያለችው የግብ ማሻሻያ እርመጃዎቿ በታሰበው ልክ እየሄደ ይገኛል ሲል አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ማወደሱን መዘገባችን ይታወሳል።
አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ለኢትዮጵያ በአራት ዓመታት የ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የተራዘመ የብድር ለመስጠት መወሰኑን እና እስከ ቅድብ ግዜያት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊየን ዶላር መልቀቁን የተመለከቱ ዘገባዎች ማቅረባችንም ይታወሳል። አስ