![](wp-content/uploads/2025/01/475266783_1053063953518739_4874885741515372822_n-1080x645.jpg)
አዲስ አበባ፣ ጥር 23 /2017 ዓ/ም፦ የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር በአንዳንድ ክልሎች “ጫናዎችን ተቋቁመው” ስራ እየሰሩ ያሉ ሀኪሞች ክፍያ አልተሰጠንም ሊከፈለን ይገባል በማለት ጥያቄ በማቅረባቸው ለእስር መዳረጋቸውን አስታወቀ።
ከተመሰረተ 77 አመታትን ያስቆጠረው ማህበሩ ከየካቲት 14 – 15/ 2017ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚያካሄደውን 61ኛው ዓመታዊ የሕክምና ጉባኤና ዓለም አቀፍ የጤና አዉደ ርዕይ አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “የሃገራችን ሀኪሞች ብዙ ጫናዎችን ተቋቁመው ስራ እየሰሩ ቢሆንም የሰሩት የዱዩቲ ክፍያ አለመከፈል የታዩበት ዓመት ነበር” ሲል ገልጿል።
አክሎም “በአንዳንድ ክልሎች ክፍያ አልተሰጠንም፣ ሊከፈለን ይገባል በማለት ጥያቄ የሚያቀርቡ ሐኪሞችም ለእስር የሚዳረጉበት ሁኔታዎች ነበሩ” ብሏል፡፡
መግለጫው የሐኪሞች የስራ አጥነት ቁጥርም እየጨመረ ከመምጣቱ በተጨማሪ በተለያዩ “በሽታዎች ተይዘው ከፍተኛ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሐኪሞቻችን ተገቢውን ሕክምና በፍጥነት ባለማግኘታቸው የሕይወት ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ” ሲል ገልጿል፡፡
በዚህ ዙሪያ ማህበሩ ከሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ጋር ምክክር ለማድረግ ቢሞከርም አሁንም ከችግሩ ስፋት አንጻር የብዙዎችን ተግባራዊ ምላሽ ይሻል ብሏል፡፡
“በኢትዮጵያ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ደህንነት አሁናዊ ሁኔታና አማራጭ መፍትሄዎች” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው አመታዊ የህክምና ኮንፈረንስም፤ ሐኪሞች ብቻ ሳይሆን እንደአጠቃላይ የጤና ባለሙያው እያጋጠመው ያለውን ማህበራዊ ጫና እና ይህ የሚያስያስከትለው ሀገራዊ ቀውስ በሃገራችን ከሚገኙ እውቅ የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ምክክር እንደሚካሄድበት ተመላክቷል፡፡
በጉባዔውም ከ400 በላይ የህክምና ባለሙያዎችን እና ከውሳኔ ሰጪዎች በተጨማሪ ከሁሉም ክልል የሚመጡ የማህበሩ አባላት ተወካዮች፣ ከተለያዩ የጤና ባለሙያዎች ማህበራት የተውጣጡ ተወካዮች፣ የህክምና ኮሌጅ ኃላፊዎች እና የመንግስት አካላት ጨምሮ ይሳተፋሉ ተብሏል። ዓለም አቀፍ የጤና አዉደርእዩም ከ70 በላይ ድርጅቶች የሚሳተፉበት ሲሆን ከ2,000 በላይ ሰዎችም ይጎበኙታል ተብሎ ይጠበቃል ብሏል።
አዲስ ስታንዳርድ በተለያዩ አካባቢዎች ለህክምና ባለሙያዎች ደመወዝ እና የትርፍ ሰዓት ክፍያ ባለመፈጸሙ ስራ ማቆማቸን መዘገቡ ይታወቃል።
በታህሳስ ወር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ካምባ ወረዳ የሚገኘው ብቸኛው የካምባ ወረዳ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፤ በክፍያና ጥቅማጥቅም አለመፈጸም እንዲሁም “በወረዳው አመራር ያልተገባ ድርጊት” ምክንያት የሕክምና ባለሙያዎች ከሥራ በመልቀቃቸው በተከሰተ የባለሙያ እጥረት ህብረተሰቡ ለከፍተኛ እንግልት መዳረጉ ይታወሳል።
ሆስፒታሉ በአከባቢው ብቸኛ የሕዝብ መገልገያ የጤና ተቋም በመሆን ለካምባና ለጋርዳ ማርታ ወረዳዎች ግልጋሎት ሲሰጥ ቢቆይም 3 ሃኪሞች በቻ በመቅረታቸው የሕክምና አገልግሎት ወደ ማቆም ተቃርቧል ሲሉ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን ከ300 በላይ የሾኔ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሠራተኞች፣ ከግንቦት እስከ ሐምሌ ድረስ ደመወዛቸው ስላልተከፈላቸው ሆስፒታሉ አገልግሎት ማቆሙን በወቅቱ አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡
በሃዲያ ዞን አከባቢዎች ከደመወዝ አለመከፈል ጋር ተያይዞ ቅሬታ እና ተቃውሞ ባሰሙ ሰዎች ላይ ማስፈራራት፣ ዛቻ፣ ድብደባ እና ለተለያዩ ጊዜያት እስራት ጭምር እንደደረሰባቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ታህሳስ 13 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ኢሰመኮ ተገቢ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ለሠራተኞች ደመወዝ ወቅቱን ጠብቆ መከፈሉን እና ሰብአዊ መብቶቹ መከበራቸውንና መጠበቃቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል ሲል አሳስቧል። አስ