![](wp-content/uploads/2025/02/OLA-Members-Photo-social-media-1024x576-1.jpg)
አዲስ አበባ፣ ጥር 27/ 2017 ዓ/ም፦ የኬንያ ፖሊስ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ላይ ‘ልዩ የፀጥታ ዘመቻ’ መጀመሩን ማስታወቁን ተከትሎ ታጣቂ ቡድኑ “ከወንጀል ድርጊቶች ጋር ግንኙነት እንደሌለው” በመግለጽ የኬንያን ሉዓላዊነትና ግዛታዊ አንድነት ሙሉ በሙሉ እንደሚያከብር ገለጸ።
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ “ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት የደቡብ እዝ ኃይላችን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በስፋት እንቅስቃሴ ያደርጋል” ሲል ገልጾ የተቀረው 5 በመቶ በድንበር አቅራቢያ እንደሚገኝ ጠቁሟል። ቡድኑ በመግለጫ”ለቦረና እና ለሌሎች ወንድማማች የኬንያ ማህበረሰቦች ደህንነት እና ጸጥታ” ያለውን ቁርጠኝነት ገልጿል።
ቡድኑ ይህን የገለጸው የኬንያ ብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት ትናንትር ባወጣው መግለጫ፤ በማርሳቢት እና ኢሲዮሎ ግዛቶች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚጠቀምባቸውን መደበቂያዎች ለቆ እንዲወጣ ለማድረግ “ ‘ልዩ የፀጥታ ዘመቻ’ መጀመሩን ማስታወቁን ተከትሎ ነው።
የኬንያ ፖሊስ በከፍተኛ ደረጃ የሚካሄደው ዘመቻ ለኬንያ ብሔራዊ ደህንነት ከፍተኛ ስጋት የሚጥሉ ህገወጥ ስራዎችን በሚያከናውኑ ወንጀለኞች ላይ ያነጣጠረ ነው ብሏል። በታጣቂው የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊት የጦር መሳሪያ፣ የአደንዛዥ ዕፅ እና የሰዎች ዝውውር፣ ህገወጥ የማዕድን ማውጫ፣ የጎሳ ግጭቶችን ማነሳሳት እና በተለይም በሶሎሎ፣ ሞያሌ፣ ሰሜን ሆር እና ሜርቲ ንዑስ ግዛቶች ውስጥ የቤዛ ክፍያ መጠየቅ የሚደረጉ እገታዎችን ያካትታል ሲልም ገልጿል።
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በመግለጫው በክልሉ ውስጥ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና በሕገወጥ ንግድን ያካተተ “ድንብር ዘለል የወንጀል መረቦች” መኖሩን ገልጾ፤ “የኢትዮጵያ መንግስት ጦር እና የመረጃ አገልግሎት ከፍተኛ ባለሥልጣናት” እነዚህን ተግባራት በማመቻቸት ተግባር ከሷል። የኦነሠ አባል በድርጊቱ ተባባሪ ሆኖ ከተገኘ ቡድኑ “እርምጃ እንደሚወስድ” አስታውቋል።
ቡድኑ አክሎም “በድንበሩ ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን ለመቅረፍ ከኬንያ ባለሥልጣናት ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ መሆኑን” ገልጿል።
በተጨማሪም የኬንያ ባለሥልጣናት “በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንዳይታለሉ” አስጠንቅቅሷል። ቡድኑ ባለስልጣናቱ “በኢትዮጵያ አገዛዝ ውስጥ ያሉ ተክክለኛ ወንጀለኞችን” ከተጠያቂነት ለማሸሽ “የተቀነባበረ ትርክት” እየፈጠሩ ነው ሲል ወቅሷል። ኬን ያለክልላዊ መረጋጋት “የተመጣጠነ እና ገንቢ ተሳትፎን” እንድትቀጥልም አሳስቧል።
ባሳለፍነው አመት ነሃሴ ወር የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኬንያና ድንበር አካባቢ “ዜጎችን የማገት፤ ንብረት የመዝረፍ የማውደምና ህገወጥ ማዕድን የማውጣትና ማዘዋወር” ተግባራት እየፈጸመ መሆኑን እና ከሶማሊያው “አልሸባብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው” የኢትዮጵያ እና የኬኒያ የመረጃ ተቋማት ማስታወቃቸው ይታወሳል።
ተቋማቱ በወቅቱ ባደረጉት በውውይታቸው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በኢትዮጵያ እና በኬንያ ድንበር እና በኬኒያ ውስጥ “ዜጎችን የማገት፤ ንብረት የመዝረፍ የማውደምና እንዲሁም የሰዎችን እንቅስቃሴ የማስተጓጎል” ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ቡድኑ “የኮንትሮባንድ ንግድ፤ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፤ ህገወጥ የማዕድን ማውጣትና ማዘዋወር” ስራዎች ላይ መሰማራቱንና ይህንንም ለማስቆም የኢትዮጵያ እና የኬኒያ የመረጃ ተቋማት አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ተጠቁሟል።
“ሁለቱ የሽብር ቡድኖች” በአካባቢው እና በቀጣናው የደቀኑትን የሽብር ስጋት በጋራ ለመከላከልና ለመቀልበስ ይረዳ ዘንድ የተቀናጀ ኦፐሬሽን አጠናክረው ለመቀጠል መወሰናቸውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመልክቷል፡፡አስ