ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በአፋር ክልል በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ከስምንት በላይ ሰዎች ተገደሉ፤ ነዋሪዎች የጅቡቲን መንግስት ተጠያቂ አድርገዋል

አዲስ አበባ፣ ጥር 24/ 2017 ዓ/ም፦ በአፋር ክልል በኢትዮ-ጂቡቲ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ኤሊዳዓር ወረዳ ሲያሩ ቀበሌ  ሀሙስ ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም በተፈፀመ የድሮን ጥቃት ቢያንስ ስምንት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ ነዋሪ ጥቃቱ ሌሊት ላይ በተከታታይ መፈጸሙን ገልጸው በጥቃቱ ከስምንት በላይ ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ የተጎጂዎች ትክክለኛ ቁጥር እስካሁን አልታወቀም ብለዋል።

ከሟቾቹ መካከል አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት እና ሁለት ወንድማማቾች የሚገኙበት ሲሆን ቢያንስ አራት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው፤ ሁለቱ በአሁኑ ወቅት በዱብቲ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ነዋሪው ተናግረዋል።

ነዋሪው ከሞቱት ሰዎች መካከል መሐመድ አይዳሂስ፣ ጋማ አሊ ኦርቢስ፣ ካኮ አሊ ኦርቢስ፣ አሊ መሐመድ ካኮ እና አይሻ ባዱል አሊ የተባሉ ግለሰቦች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ማይራም መሐመድ አብደላ፣ ፋቱማ አሊ ሀመድ እና አሊ መሐመድ አሊ የተባሉ ግለሰቦች በጥቃቱ መቁሰላቸውን ገልጸው ሆኖም የተጎጂዎች ዝርዝር ሙሉ ለሙሉ እስከአሁን አለመታወቁን ገልጸዋል።

ነዋሪው ጥቃቱ የተፈፀመው “በጅቡቲ መንግስት” እንደሆነ በመግለጽ “ድሮኖች አካባቢውን ዒላማ ሲያደርጉት በሁለት ወራት ውስጥ ለኹለተኛ ጊዜ ነው” ብለዋል።

አክለውም ጥቃቱ የተፈፀመው የጅቡቲ መንግስት ተቃዋሚ በሆነው እና ራሱን አንድነትና ዴሞክራሲ አስመላሽ ግምባር (FRUD) ብሎ የሚጠራው ቡድንን ለማጥቃት በሚል ነው ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ምንጭ በበኩላቸው ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በነበራቸው ቆይታ “የጂቡቲ ባለሥልጣናት፤ የቡድኑ ታጣቂዎች በድንበር አካባቢ እንዳሉ በመግለጽ ታጣቂ ቡድኑን ለማጥቃት በማስመሰል የአከባቢው ነዋሪዎችን ከክልሉ በኃይል ለማስወጣት የሚደረገው ጥረት አካል ነው” ሲሉ ጥቃቱ የአካባቢውን ህዝብ ዒላማ ያደረገ መሆኑን ይናገራሉ።

በአገሪቱ የሚንቀሳቀሰው የጂቡቲ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ (LDDH) የተሰኘው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት በበኩሉ “አራት ሴቶችን ጨምሮ 14 ሰዎች መገደላቸውን” እና “ሴቶችን እና ህጻናትን” ጨምሮ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን በመግለጽ ጥቃቱ እጅግ የከፋ መሆኑን አስታውቋል።

የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ “ሌሊቱን ሙሉ የአርብቶ አደሮች ካምፖችን በቦምብ ማጋየታቸውን ቀጥለዋል” በማለት ተጨማሪ ጉዳት መድረሱን አመልክቷል።

ድርጅቱ ትናንት ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ጥቃቱን “በአፋር ሕዝብ ላይ ሆን ተብሎ የተፈጸመ የጦር ወንጀል” በማለት አውግዞት “ቱርክ እና ቻይና ድሃ የሆነውን የአከባቢው አርብቶ አደር ማኅበረሰብ እየገደለ ላለው የጂቡቲ መንግስት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እስከመቼ ያስታጥቁታል” በማለት ለጂቡቲ ወታደራዊ ኃይል የሚደረገውን የውጭ ድጋፍ ጥያቄ ውስጥ አስገብቷል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጂቡቲ መንግስት እና ራሱን አንድነትና ዴሞክራሲ አስመላሽ ግምባር (FRUD) ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል ያለው ውጥረት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ታጣቂ ቡድኑ በፀጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት በመፈፀም ተወንጅሏል።

በጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 2022 የጂቡቲ መከላከያ ሚኒስቴር በታጁራ ክፍለ-ጦር ላይ በተፈፀመ ጥቃት ሰባት ወታደሮች መገደላቸውን አስታውቆ “በወንጀሉ ተሳታፊ የሆኑትን ለመያዝ እየሰራሁ ነው” ሲል ገልጾ ነበር

በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት ጥቃቱን “አረመኔያዊና የፈሪነት ተግባር” ሲል አውግዞ ጂቡቲ ለሚያጋጥሟት የደህንነት ስጋቶች ምላሽ ለመስጠት “ሙሉ በሙሉ ዝግጁ” መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቆይቶ ባወጣው መግለጫ፣ በአፋር ክልላዊ መንግሥት ትብብር “ስድስት የጅቡቲ ወታደሮችን ከታጣቂ ቡድኑ እጅ ማስለቀቁን” አስታውቋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button