ዜናፖለቲካ

ዜና፡ ምክር ቤቱ አቶ ብርሃኑ አዴሎን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አድርጎ ሾመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22 2017 ዓ.ም:- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባ አቶ ብርሃኑ አዴሎን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አድርጎ ሾመ። 

ምክር ቤቱ አቶ ብርሃኑ አዴሎ ተቋሙን ለመምራት በትምህርት ዝግጁነትና በሥራ ልምድ “ብቁ ሆነው የተገኙ” መሆናቸውን በመማመን ሹመቱን በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።

የቀድሞውን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለን (ዶ/ር) በመተካት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር በመሆን ዛሬ ጥር 22 ቀን 2017 የተሾሙት አቶ ብርሃኑ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ዘመነ መንግስት የሚኒስትሮች ካቢኔ ሚኒስትር እና ከፍተኛ አማካሪ በመሆን አገልገለዋል።

በተጨማሪም በተለያዩ መንግሥታዊ ኃላፊነቶች ላይ የሠሩት አቶ ብርሃኑ አዴሎ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ከኃላፊነታቸው እስከተነሱበት ደረስ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ነበሩ። ይህም የመጨረሻ መንግሥታዊ ኃላፊነታቸው ነበር። 

በወቅቱ አቶ ብርሃኑ “ከሠራተኞች እና ከተቋሙ ደንበኞች ቅሬታዎች ይቀርቡባቸው እንደነበር” እና በዚህም ምክንያት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኃላፊነት ማንሳታቸውም የሪፖርተር ዘገባ አመላክቷል።

በመንግሥታዊ ተቋማት ከነበራቸው ኃላፊነት በተጨማሪም የ1997 ምርጫ ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነበሩ።

ከመንግስታዊ የሥራ ኃላፊ ከተነሱ በኋላ ላለፉት አስር ዓመታት በጥብቅና እና በህግ ማማከር ስራ ላይ መሰማራታቸውን ለፓርላማ አባላት የቀረበው የስራ ልምድ ያሳያል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አቶ ብርሃኑ አዴሎ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ከሕንድ አገር የማስተርስ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር የነበሩት ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) “የሥራ ጊዜያቸውን በማጠናቀቃቸው” መሰናበታቸውን ተከትሎ ምክትል ኮሚሽነር የነበሩት ራኬብ መለሰ ጊዜያዊ ኮሚሽነር ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወቃል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button