![](wp-content/uploads/2025/02/DG-TPLF-edited-1200x645.jpg)
አዲስ አበባ፣ ጥር 29/2017 ዓ.ም፡- በደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ቡድን የትግራይ ህዝብ እና የትግራይ ልሂቃን ቀዳሚ ምርጫው ሰላም ነው ሲል ትላንት ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ጠ/ሚኒስት አብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከቀናት በፊት ጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ለትግራይ ህዝብ በተለይ ለትግራይ ሊሂቃን ሲሉ ባቀረቡት ጥሪ የክልሉ ህዝብ በተደጋጋሚ ጦርነቶ ተጎጂ እንደነበር በመጥቀስ ህዝቡ ወደ ልማትና ማገገም እንዲመለስ አብረን እንስራ ማለታቸው ይታወሳል።
ህወሓት የጠ/ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ ትላንት ጥር 28 ቀን መግለጫ ያወጣ ሲሆን በመግለጫውም የትግራይ ህዝብ ቀዳሚ ምርጫ ሰላም ነው ሲል በመግለጽ የትግራይ ህዝብን የሰላም ምኞት አውን ለማድረግ ሁሉመ ገንቢ ሚና ይጫወት ሲል ጠይቋል፤ ከማንኛውም አካል ጋር በሰላም ዙሪያ ለመስራት ዝግጁ ነኝ ሲል አስታውቋል።
“ከሁሉም ሰላም ፈላጊ ሀይል ጋር ለመስራት ትላንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ ዝገጁ መሆናችንን ማረጋገጥ እንፈልጋለን” ብሏል።
ጠ/ሚኒስትር አብይ ባስተላለፉት መልዕክት ለዘመናት የትግራይ ህዝብ በጦርነት ማሳለፉን አውስተው በተለይም ግን ባለፉት መቶ አመታት ከማዕከላዊ መንግስቱ ጋር በተለያዩ አጋጣሚዎችን እና ምክንያቶች ግጭቶች ውስጥ መግባቱን በመግለጽ ጉዳት ማስተናገዱን አመላክተዋል፤ “የትግራይ መሬት የጦር አውድማ ሆኗል፤ የትግራይ ህዝብም የጦርነት መጠቀሚያ ሆኗል” ብለዋል።
በመሆኑም የክልሉ ልሂቃን “ትግራይና ህዝቦቿ ከጦርነቱ ያገኙት ወይስ ያጡት ጥቅም ይበዛል ብሎ መጠየቅና መልስ ማግኘት አለበት” ሲሉ አሳስበዋል።
ህወሓት በመግለጫው ባለፉት መቶ አመታት የትግራይ ህዝብ ያደረጋቸው ጦርነቶች “ህልውናውን ለማረጋገጥ እና ለጭቆና አጅ አልሰጥ በማለት ነው” ሲል በመግለጽ “የትግራይ ህዝብ ያደረጋቸው ተጋድሎዎች ያኮሩታል እንጂ አያስቆጩትም” ብሏል።
የትግራይ ህዝብ እና ልሂቃን ያደረጓቸው ተጋድሎዎች “ለሉዓላዊነቱ፣ ለነፃነቱና ለክብሩ ያደረጋቸው ታጋድሎዎች ናቸው፤ እንደ ብሔር እና ህዝብ የመኖር እና ያለመኖር ሁኔታውን የወሰኑ ወሳኝ ምዕራፎች ነበሩ” ብሏል። ይህ ማለት ግን “የትግራይ ህዝብ የጦርነት ባህል ኖሮት አይደለም” ሲልም ገልጿል።
“መቆጨት ያለባቸው ሀገር እና ስርአት ለመትከል መስዋዕትነት በከፈለው የትግራይ ህዝብ ላይ ባእዳውያንን በመጋበዝ ያስጨፈጨፉት ስርአቶች ናቸው” ብሏል።
“የትግራይ ህዝብ እና ለሂቃን በኢትዮጵያ ታሪክ ዋነኛ ታዋናይ የነበሩ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ስርአቶች እንዲገለሉ እና እንደ ሁለተኛ ዜጋ እንዲኖሩ ለማድረግ ያልተደረገ ነገር የለም” ሲል ገልጿል። ማሳያናቸው በሚልም ከአጼ ሀይለስላዜ ዘመነ መንግስት እስከ አሁን ድረስ በነበሩ ማዕከላዊ መንግስታት ህዝቡ ደረሰበት ያለውን በዝርዝር ጠቅሷል።
አሁንም ቢሆን የትግራይ ህዝብ ለሰላም ቁርጠኛ መሆኑን በተለያየ መንገድ እያረጋገጠ ይገኛል ያለው የፓርቲው መግለጫ “የትግራይ ህዝብ ለሰላም ጥብቅ ምኞት ስላለው ብቻ የዘር ማጥፋት ያደረሰበትን ጦርነት ያስቆመውን የፕሪቶርያ ስምምነት ተቀብሎ ለሙሉ ተፈጻሚነቱ ለሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ጥሪ እያስተላለፈ ይገኛል” ብሏል።
“የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ተግባሪው ሊሆን አልቻለም፣ መሬት ላይ አልወረደም” ያለው መግለጫው የትግራይ ህዝብ ሰላም በተግባር እንዲታጀብ ፍላጎት እና ድጋፍ ያደርጋል ሲል አስታውቋል።
“ሰላማችንን ለማስፈን እና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ባለን አቅም ሁሉ የምንሰራበት ጉዳይ መሆኑን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፤ እያንዳንዷ የሰላም ጥሪ እንዳትጨናገፍ እንሰራለን” ብሏል።
“ከወራሪ ሀይሎች ነጻ ያልወጣ ህዝባችን ነጻ እንዲወጣ ማድረግ፣ የተፈናቀለው ህዝባችን የመኖር ዋስትናው ተረጋግጦለት ወደቀየው እንዲመለስ ማድረግ፣ የክልሉ ግዛታዊ አንድነት እንዲጠበቅ ማድረግ በህዝቡ ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ የፈጸሙበትን ሀይሎች ተጠያቂነታቸውን ማረጋገጥ ለቀጣዩ የትግራይ ህዝብ ሰላም ወሳኝ ናቸው” ብሏል።
“በዚህም ትግራይን ወደ መደበኛ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መመለስ የትግራይ ሕዝብ ፍላጎትና የህወሓት መርህ ነው” ሲል ገልጿል። አስ