ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና: የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እርዳታ ማቋረጡ ኢትዮጵያ በኤች አይ ቪ ላይ የምታደርገውን ትግል አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት አስታወቀ

ከሩብ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የቫይረሱ ተጠቃሚዎችን ለአደጋ ያጋልጣል ሲል አስጠንቅቋል

አዲስ አበባ፣ ጥር 29/2017 ዓ.ም፡- ከኤች አይ ቪ/ኤድስ ጋር በተያያዘ የአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ድጋፍና እርዳታ መቋረጥ በኦሮሚያ እና ጋምቤላ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ከ270 ሺ በላይ ለሚሆኑ የቫይረሱ መከላከያ መድሃኒት ተጠቃሚዎችን ህይወት ይበልጥ ከባድ ያደርገዋል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤች አይ ቪ/ኤድስ ፕሮግራም አስጠንቀቀ።

ተቋሙ ትናንት ረቡዕ ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው ወቅታዊ መረጃ እንዳስታወቀው የአሜሪካ መንገሰት ለኤች አይ ቪ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ለሆኑ ለወጣቶችና ለልጃገረዶች፣ ለአካባቢያዊ ፕሮግራሞች እንዲሁም ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሰጠውን ድጋፍ ማቋረጡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወሳኝ የሆኑ አገልግሎቶችን እንዳያገኙ ሊያደርጋቸው ይችላል ብሏል።

ከእነዚህ አገልግሎቶች መካከልም የኤችአይቪ ምርመራ፣ የጸረ-ኤድስ ሕክምና፣ የኤችአይቪ ቅድመ-ተጋላጭነት መከላከያ እንዲሁም የሳንባ ነቀርሳ ምርመራ እና በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች እና በጾታ ላይ የተመሠረተ ጥቃትን ለመቅረፍ የሚደረጉ ድጋፎች ይገኙበታል።

ዩናይትድ ስቴትስ የምትሰጠውን እርዳታ በማቆሟ ምክንያት በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ እና ጋምቤላ ክልሎች የአገልግሎት መቋረጥ ማስከተሉን የጠቆመው ፕሮግራሙ ከ235 ሺህ በላይ ሰዎች አዲስ የኤች አይቪ ኢንፌክሽንና በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል የሚውል የኮንዶም ስርጭት ከአሁን በኋላ አይደርሳቸውም ብሏል።

በተጨማሪም በድምሩ 18 ሺ 75 የሚሆኑ ተጠቂዎች የጤና እና እንክብካቤ አገልግሎቶች ድጋፍ አያገኙም ተብሏል።

እንዲሁም ተጨማሪ 2 ሺ 385 ሰዎች የጸረ ኤችአይቪ፣ የሳንባ ነቀርሳ እና በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖችን ህክምና ማግኘት እንደማይችሉ ተመላክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በቅርብ ሳምንታት ያስተላለፉት መመሪያ: የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት እና እንደ ዩ.ኤን.ኤድስ ያሉ አጋሮቹን ጨምሮ የሰብአዊ ድርጅቶች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ጥርጣሬ ፈጥሯል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሮቢዮ በበኩላቸው በ90 ቀናት የውጭ ዕርዳታ ግምገማ ጊዜ ውስጥ “አስቸኳይ የህይወት አድን የሰብአዊ ዕርዳታ ፕሮግራሞችን” እንደሚቀጥሉ ገልጸው ነበር።

ሆኖም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤች አይ ቪ/ኤድስ ፕሮግራም የስራ ማቆም ትእዛዙን ተከትሎ በጤና መረጃ አስተዳደር ስርዓት ውስጥ የጸረ ኤች አይቪ መረጃን በማስገባት ረገድ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ 10 ሺ የሚደርሱ የመረጃ ሰራተኞች የስራ ውል መቋረጥ ምክንያት በኢትዮጵያ የጤና መረጃ ስርዓት “በከፋ ሁኔታ” ሊጎዳ ይችላል ሲል አሳስቧል።

በተለይም ክትትል በሚፈልጉ ኬዞች ላይ ችግር እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።

በተጨማሪም የገንዘብ ድጋፍ መቋረጡ የአካባቢ ጤና አጠባበቅ አቅም ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንዳያደናቅፈው ስጋት እንዳለው አስታውቋል።

የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡት ስልጠና ላይ ተፅዕኖ በማሳደር በኢትዮጵያ የኤችአይቪ በሽታ መከላከል ሂደት ላይ እየተመዘገበ ያለውን እድገት ያዘገየዋል ሲል አመልክቷል።

ዩ.ኤን ኤድስ  ይህን ያስታወቀው በአሜሪካ መንግስት በጀት ድጋፍ ስር ከተቀጠሩ ሰራተኞች የተያያዙ ሁሉም እንቅስቃሴዎች እና ክፍያዎች እንዲያቋርጡ የጤና ሚኒስቴር መመሪያ ከሰጠ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነው።

መመሪያው ወደ አምስት ሺየሚጠጉ ሰራተኞች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ሪፖርቶች ጠቁመዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤች አይ ቪ/ኤድስ ፕሮግራም በወቅታዊ መረጃው የፋይናንስ እገዳው የኤችአይቪ ምርመራ መሳሪያዎችን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ የኤችአይቪ አገልግሎቶችን በማቅረብ ሂደት ላይ “ከፍተኛ መዘግየት” እንደሚያስከትል አመልክቷል።

በጎርጎሮሳውያኑ 2023 የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት አስቸኳይ ጊዜ የኤችአይቪ/ኤድስ ምላሽ ዕቅድ (PEPFAR)  በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ምላሽ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ኢንቨስት እንዳደረገ ከኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ በጎርጎሮሳውያኑ 2003 የተቋቋመው ይህ ፕሮግራም በግምት 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎችን አስፈላጊ የኤች አይ ቪ ምርመራ እና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ ያስቻላቸው ሲሆን ከ349 ሺ በላይ የሚሆኑ ወላጅ አልባ ሕፃናት በየዓመቱ አስፈላጊ እንክብካቤ እና ድጋፍ አግኝተዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button