![](wp-content/uploads/2025/02/photo_2025-02-06_15-52-31.jpg)
አዲስ አበባ፣ ጥር 29/ 2017 ዓ/ም፦ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት የጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ዋርድ ባሳለፍነው ሳምንት በተገደለው ዶ/ር አንዱአለም ዳኘ ስም እንዲሰየምና በሆስፒታሉ ግቢ ሓውልት እንዲቆምለት ወሰነ። በግድያው ላይም ጥልቅ ምርመራ እንዲደረግ እና እጃቸው ያለበት አካላት በአፋጣኝ ለህግ እንዲቀርቡ እንዲደረግ ጠይቋል።
ዩኒቨርቲው ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ የ37 አመቱ ዶ/ር አንዱአለም ምንም እንኳን “የተሰጠውን ጸጋ ሳይሰስት በመጠቀም ለበርካቶች የዘርፉ ባለሙያዎችና በሙያው ላገለገላቸው በርካታ ህሙማን የቅን አገልጋይነት ተምሳሌት የነበረ እንቁ ባለሙያ ነበር” ብሏል።
አክሎም የቀረቡለትን በርካታ ዓለምአቀፍ የስራ ቅጥር ግብዣዎች ባለመቀበል ወገኑን ለማገልገል ቆርጦ የነበረ ባለሙያ ከመሆኑም በላይ በሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና ክፍሉን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማሻሻል እየጣረ የነበረ እና እውን ለማድረግ ጫፍ ላይ ደርሶ ያለፈ መሆኑንም ገልጿል።
ዶ/ር እንዱአለም በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ታሪክ “የመጀመሪያውን ቀዶ ጥገና ስራ መስራቱን” የገለጸው ዩኒቨርሲቲው እስከ ህልፈቱ ድረስ ሆስፒታሉ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እንደነበርም አስረድቷል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራር ከዩኒቨርሲቲው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አመራር አካላት ጋር የዶ/ር አንዱአለም ዳኘን ህልፈት ተከትሎ መሰራት ባለባቸው ስራዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት አካሄዶ የተለያዩ ወሳኔዎችን ማሳለፉንም አስታውቋል።
በዚህም የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቀዶ ጥገና ዋርድ፤ “ዶ/ር አንዱአለም ዳኘ ቀዶ ጥገና ዋርድ” ተብሎ በስሙ እንዲሰየም እና ሃውልት እንዲቆምለት ወስኗል።
ባለቤቱ ከትምህርት ዝግጅት አንጻር በሲቪል ምህንድስና 2ኛ ዲግሪ ያላት እና ጥሩ አቅም ያላት በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል የምትቀጠርበት ሁኔታ እንዲመቻች ውሳኔ መተላለፉን አስታውቋል።
በተጨማሪም ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ ስኩል ኦፍ ሜዲሲን ውስጥ በስሙ ስኮላርሺፕ (BDU Talent Scholarship) እንዲቋቋም መወሰኑም ተገልጿል።
ዩኒቨርሲቲው በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ አቶ አድነው በለጠ በቅርቡ የተገደሉ ሌላ የህክምና በለሙያ መሆናቸውን ገልጾ የሚመለከታቸው አካላት በጉዳዩ ላይ ተገቢውን እና ጥልቅ ምርመራ አድርገው በግድያው ላይ እጃቸው ያለበትን አካላት በአፋጣኝ ለህግ እንዲቀርቡ እንዲደረግ ጠይቋል።
በአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባህር ዳር የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ህክምና ክፍል ዳይሬክተር የነበሩት ዶ/ር አንዱአለም ዳኜ ባሳለፍነው ሳምንት ጥር 24/2017 ዓ.ም ከስራ አምሽተው ወደ ቤታቸው በመጓዝ ላይ ሳሉ በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸው ይታወሳል፡፡ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ዶክተሩ የተገደሉት “በዘራፊዎች ሳይሆን አይቀርም” ማለቱን የአሜሪካ ድምጽ ዘግቧል።
የመምሪያው ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ዶክተሩ በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሥር ባለው ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝ ሆስፒታል ቅጽር ግቢ ውስጥ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በመሄድ ላይ ሳሉ በከተማዋ ሰባታሚት “ቆሸ” በተባለ ሥፍራ በታጣቂዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ህይወታቸውን አጥተዋል ብለዋል።
በአካባቢው ለዝርፊያ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ቡድን እንዳለ ያመለከቱት ኮማንደሩ ገዳዮችን ለመያዝ ብዛት ያለው የፀጥታ ኅይል ተሰማርቷል ብለዋል።
የአማራ ክልል የጤና ባለሙያዎች ማህበር በበኩሉ በህክምና ባለሙያዎች ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ እና እስር እያሳሰበው እንደሆነ ተናግሯል ።
ይህ በእንዲህ አንዳለ የኢትዮጵያ የጤና ሚንስቴር በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ በዶክትር አንዱ ዓለም ዳኘ ሕልፈተ ህይወት ሐዘኑን ገልጾ ሕብረተሰቡን በቅንነት እና በታታሪነት የሚያገለግሉ የጤና ባለሙያዎች ላይ የሚደረግ ግድያ ተቀባይነት የሌለው እና የሚወገዝ ተግባር ነው” ብሏል። አስ