ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ የዩኤስኤድ እርዳታ መቋረጥ ለበርካታ ሰራተኞች ስራ የማጣት ስጋት እንደፈጠረባቸው ምክር ቤቱ ገለጸ፤ መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲያደርግም ጠይቋል

በይስሓቅ እንድሪስ @Yishak_Endris

አዲስ አበባ፣ ጥር 30/ 2017 ዓ/ም፦ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤድ) የሚሰጠውን እርዳታ እና ድጋፍ በአስቸኳይ ማቋረጡን ተከትሎ በርካታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሰራተኞች ስራ የማጣት ስጋት እንደተደቀነባቸው በመግለጽ መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጠየቀ።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህመድ ሁሴን ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ በአሁኑ ሰዓት በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ስር በአጠቃላይ 5300 የሚደርሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንደተመዘገቡ ገልጸው፤ በዩኤስኤድ ሙሉ በሙሉ እና በከፊል የበጀት ድጋፍ ሲያገኙ የነበሩ ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀኑን ተናግረዋል።

“አንዳንዶቹ ከዩኤስኤድ እርዳታ የሚያገኙ አሉ። ሌሎቹ ደግሞ ከኤምባሲዎች፣ ከአለምአቀፍ ተቋማት ድጋፍ የሚያገኙም አሉ። ነገር ግን ከዩኤስኤድ በአብዘሃኛው እና ሙሉ በሙሉ ፈንድ የሚደረጉም አሉ። እነሱ በከፍተኛ ደረጃ ሊጎዱ ይችላሉ”ብለዋል።

አክለውም “እርዳታው በድንገት መቋረጡ” ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ብቻ ሳይሆን እነሱ የሚያገለግሉት ማኅበረሰብ በዋነኝነት የመጀመሪያው ተጎጂ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ ሰራተኞችም ደመወዝ የሶስት እና የአራት አመታት ኮንትራት ወስደው ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው ዩኤስኤድ የሚሰጠውን እርዳታ ማቋረጡን ተከትሎ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ለሰራተኞች የሚከፈል ደመወዝ ላይኖር እንደሚችል እና ኮንትራት ማቋረጥ ሂደት ውስጥ መገባቱን አስረድተዋል።

አሃዛዊ መረጃን በተመለከተ አሁን ላይ በሂደቱ ምን ያህል ተቋማት እንደሚጎዱ የተጨበጠ መረጃ ለመስጠት ሁሉም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ምን አይነት ፕሮጀክቶችን ሲሰሩ እንደነበር፣ ለፕሮጀክቱ የተመደበው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ፣ ምን ያህል የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚዎች እንዳሏቸው እና ምን ያህሉን ፕሮጀክት እየሰሩበት ነበር የሚለው ዝርዝር  መታወቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በጥቅሉ ሊደርስ ስለሚችለው ጉዳት  እና ለዛ ጉዳት ደግሞ ምን መደረግ እንዳለበት መነሻ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ለማድረግ መታሰቡን ጠቁመዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“ይሄ በራሱ የሚያስተምረን ብዙ ነገር ይኖራል።” ያሉት ፕሬዝዳንቱ አክለውም “የተሰጠን ሀብት አለን ከጦርነት እና ከግጭት ወጥተን ወደ ልማት መግባት አለብን” ሲሉ አበክረዋል።

“አንድ ተቋም ገንዘብ ሲሰጥህ ብቻ የምትሰራ ድጋፉ ሲቋረጥ ደግሞ የምታቆምበት ነገር መቆም አለበት እና ያንን መርህ የውይይት መነሻ ማድረግ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

አስቸኳይ የሆኑ የህይወት አድን አገልግሎቶች በመኖራቸው እና ምንም ቅድመ ዝግጅት ባልተደረገበት ሁኔታ እርዳታው በመቋረጡ መንግሥት በማሥረጃ ላይ ተመርኩዞ አስፈላጊውን የዲፕሎማሲ ስራ እንዲያከናውን ጠይቀዋል።

ለአዲስ ስታንዳርድ አስተያየታቸውን የሰጡ እና መጠሪያ ስማቸውም ሆነ የሚሰሩበት ተቋም ስም እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአንድ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ በበኩላቸው የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤድ) የሚሰጠውን እርዳታ እና ድጋፍ በአስቸኳይ ማቋረጡን ተከትሎ በርካታ ችግሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

“በተለይም አስቸኳይ የነፍስ አድን ስራዎች ጥያቄ ውስጥ ይገባሉ” ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ አክለውም በድርጅታቸው በኩል ሊደርስ ስለሚችለው ጉዳት መረጃ በማሰባሰብ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪ ድርጅቶቹ ለሰራተኞቻቸው የሚከፍሉት ደመወዝ እና ፕሮጀክት ማስኬጃ ገንዘብ ስለማይኖራቸው ተግዳሮቱ ከፍተኛ እንደሚሆን ገልጸዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ ከሰሞኑ በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤድ) በኩል የተላለፈውን የእርዳታ ማቆም ውሳኔ በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን ገልጿል።

በተጨማሪም የዩኤስኤድ ውሳኔን ተከትሎ ያለ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ግልፅ ፍቃድ ንብረት የማስተላለፍ፣ የማስወገድ ወይም የመሸጥ ወይም ከመደበኛ ፕሮጀክት ስራዎች ጋር ተያያዥ ከሆኑ ጉዳዮች ውጭ በማናቸውም መልኩ ሃብትና ገንዘብን ለሶስተኛ ወገን ማስተላለፍ የተከለከለ መሆኑን አሳስቧል።

የጤና ሚኒስቴርም ከአሜሪካ መንግሥት በሲዲሲ ወይም ዩኤስኤድ አማካኝነት በተገኘ የበጀት ድጋፍ የሚከናወን ማንኛውም ስራም ሆነ ክፍያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከጥር 24፣ 2025 ጀምሮ እንዲቋረጥ ማሳሰቢያ እንደደረሰው ገልጿል።

አዲስ ስታንዳርድ የተመለከተው እና በጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ተፈርሞ ለሁሉም የክልል ጤና ቢሮዎች የተሰራጨው ይህ ደብዳቤ “በጤና ሚኒስቴር ድጋፍ የተቀጠሩ እና ተቋማችሁ ከሲዲሲ ወይም ዩኤስኤድ ጋር በሚያደርገው ውል መሰረት የተቀጠሩ ሰራተኞችን በተመለከተ ስራ ላይ እንዲውል አሳስባለሁ” ይላል። 

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ረቡዕ ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዩኤስኤድ ፕሮጀክቶች መቋረጣቸው በኢትዮጵያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሥራ ላይ  አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን አስታውቋል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው ዩኤስኤድ ከበርካታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የልማትና የሰብአዊ ምላሽ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ዋነኛ የድጋፍ ምንጭ እንደነበር ገልጾ ይሁን እንጂ ድንገተኛ እገዳው በእነዚህ ድርጅቶች እና በሚያገለግሏቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ የማይቀር አሉታዊ ውጤት ያስከትላል ብሏል።

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ ተወካይ በመሆን ጉዳት ያጋጠማቸውን የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ እንዲሁም አማራጭ የፋይናንስ ምንጮችን እና የድጋፍ ዘዴዎችን ጨምሮ የመቋቋም ስርዓትን ለመዳሰስ ልዩ ቡድን ማቋቋሙን አመልክቷል።

እንዲሁም ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማስቀመጥ ውይይቶችን ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁሟል።

በተጨማሪም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ በትጋት እንዲሰሩ እና በተለይም በሕይወት አድን ሥራዎቻቸው ውስጥ አማራጭ የፋይናንስ ማግኛ ዘዴዎችን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርቧል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button