![](wp-content/uploads/2025/02/Kenya-OLA.jpg)
አዲስ አበባ፣ ጥር 28/2017 ዓ.ም፡- የኬንያ ብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት በማርሳቢት እና ኢሲዮሎ ግዛቶች በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ላይ እያካሄደ ባለው ‘ልዩ የፀጥታ ዘመቻ’ ከኢትዮጵያ ጋር በመቀናጀት ነው ሲል የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የኬንያ ብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ኑረዲን ሞሐመድ ሐጂን ጨምሮ የሁለቱ ሀገራት የጸጥታ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች መወያየታቸውን የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የላከውን መግለጫ ዋቢ በማድረግ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ባሰራጩት ዘገባ አመላክተዋል።
የሁለቱ ሀገራት የደኅንነትና የጸጥታ አካላት በየድንበራቸው ውስጥ በሚገኙ የቡድኑ ካምፖች ላይ የተቀናጀ ኦፕሬሽኖች እያካሄዱ እንደሚገኙ መግለጫው ማመላከቱን ዘገባዎቹ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ እና ኬንያ በቡድኑ ላይ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ማካሄድ የጀመሩት በቀጣናዊ የጸጥታ እና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የተፈራረሟቸውን ስምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግ መሆኑን ዘገባዎቹ አመላክተዋል።
በሁለቱ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉትን ሽብርተኝነት፣ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች እና የመሣሪያ ዝውውርን ለከመከላከል ተግባራዊ መሆን የጀመረው የተቀናጀ ኦፕሬሽን በዋናነት በእነዚህ እንቅስቃሴዎች የሚሳተፈውን የሸኔ ታጣቂ ከሁለቱ ሀገራት ድንበሮች አካባቢ ለማስወገድ የሚረዳ እንደሆነ መረጃው አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና የኬንያ ፖሊስ ከትላንት ወዲያ ጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም በጀመርኩት ዘመቻ በርካታ ቡድኑ ሲጠቀምባቸው የነበሩ መሳሪያዎችን እና ንብረቶችን ማርኪያለሁ ብሏል።
በርካታ መሳሪያዎችን እና ተተኳሽ ጥይቶችን ይዣለሁ ያለው የኬንያ ፖሊስ በተጨማሪም ቡድኑ ሲጠቀምባቸው የነበሩ ንብረቶችንም ማርኪያለሁ ብሏል፤ ማርኪያቸዋለሁ ካላቸው የቡድኑ ንብረቶች መካከልም ጀረሬተር፣ የፀሃይ ሀይል መጠቀሚያ ቁሳቁሶች ይገኙበታል።
ቡድኑ በኬንያ ቦረና እና በኢትዮጵያ ኦሮሞ ብሔር መካከል ያለውን የጠበቀ የቤተሰብ እና የባህል ትስስር እንደ መጠቀሚያ በመገልገል ወደ ማህበረሰቡ ዘልቆ በመግባት እና በህብረተሰቡ ውስጥ በመደበቅ ተንቀሳቅሷል ሲል የኬንያ ፖሊስ ወንጅሏል፤ በአከባቢው ማህበረሰብ ላይ ተነግሮ የማያልቅ ስቃይ እየፈጸመ ይገኛል ብሏል።
የኬንያ ፖሊስ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ላይ ‘ልዩ የፀጥታ ዘመቻ’ መጀመሩን ማስታወቁን ተከትሎ ታጣቂ ቡድኑ “ከወንጀል ድርጊቶች ጋር ግንኙነት እንደሌለው” በመግለጽ የኬንያን ሉዓላዊነትና ግዛታዊ አንድነት ሙሉ በሙሉ እንደሚያከብር መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል።
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ) ትላንት ጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት የደቡብ እዝ ኃይላችን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በስፋት እንቅስቃሴ ያደርጋል” ሲል ገልጾ የተቀረው 5 በመቶ በድንበር አቅራቢያ እንደሚገኝ ጠቁሟል። ቡድኑ በመግለጫው ”ለቦረና እና ለሌሎች ወንድማማች የኬንያ ማህበረሰቦች ደህንነት እና ጸጥታ” ያለውን ቁርጠኝነት መግለጹም በዘገባው ተካቷል። አስ