ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በምዕራብ ጎጃም ዞን በተካሄድ ውጊያ የ14 ዓመት ታዳጊና መነኩሴን ጨምሮ አራት ሰዎች ተገደሉ፤ በሰብል ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል

አዲስ አበባ፣ ጥር 27/ 2017 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን  ጃቢ ጠህናን ወረዳ ጅማት እንቆቅማ ቀበሌ አርብ ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከለ በተካሄደ “በከባድ መሳሪያ” በታገዘ ውጊያ የ14 ዓመት ታዳጊ እና መነኩሴን ጨምሮ አራት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ። በሰብል ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ የቀበሌው ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ፤ ሀሙስ ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም “የመንግሥት የጸጥታ አካላት በስፍራው የተለየ እንቅስቃሴ” ማድረጋቸውን ተከትሎ ውጥረት መጀመሩን ተናግረዋል። 

“ሀሙስ ዕለታ መከላከያ ሠራዊት ህዝቡን እህል አዋጡ እያለ በየቤቱ እየዞረ የአርሶ አደሩን ምርት ሲጭን ነው ውጥረቱ የጀመረው” ያሉት ነዋሪው በማግስቱ አርብ “በአከባቢው የሚንቀስቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች” ተኩስ መክፈታቸውን ተከትሎ ግጭት መቀስቀሱን ገልጸዋል።

ይህን ተከትሎ አርብ ዕለት ሙሉ ቀን “በሞርታር የታገዘ ውጊያ” በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሲካሄድ መዋሉን ጠቁመዋል።

በዚህም አንድ የ14 ዓመት ታዳጊ እና ሌላ በአከባቢው ነዋሪ የሆኑ መነኩሴ በተባራሪ ጥይት ተገድለዋል ያሉት ነዋሪው ሌሎች ሁለት ወጣቶች ደግሞ “የመንግሥት የጸጥታ አካላት ከቤታቸው አውጥተው ገደሏቸው” ብለዋል።

በተጨማሪም በግጭቱ መካከል በከባድ መሳሪያ በአርሶ አደሩ ሰብል ላይ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል።

ሌላኛው ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአከባቢው ነዋሪ በበኩላቸው በከባድ መሣሪያ የታገዘ ውጊያ መካሄዱንና አራት ሰዎች ህይወት ማለፉን እንደሚያውቁ ገልጸው።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በግጭቱ ከተገደሉት መካከል የ14 አመት ታዳጊ እንደሚገኝ ያረጋገጡት ነዋሪው የቀብር ስነ-ስርዓቱም በገብርኤል ቤተክርስትያን ተፈጽሟል ብለዋል።

በሰዎች ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በአርሶ አደሮች ሰብል ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት መድረሱን እኚሁ ነዋሪ አክለዋል።

“ባቅላብ የሚባል ቦታ አካባቢ የሚገኝ የአርሶ አደር ሰብል በጠቅላላ ነው የወደመው። በሞርታር ነው የተቃጠለው። የተከመረ ጤፍ ሙሉ ለሙሉ ወድሟል። ከጤፍ ሌላ ከፍተኛ የሆነ የበቆሎ ምርትም ተቃጥሏል” ብለዋል።

እኚሁ ነዋሪ አያይዘውም ግጭቱን ተከትሎ “በርካታ ወጣቶች በጸጥታ አካላት ተይዘው መወሰዳቸውንም” ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ከሰሞኑ የተሻለ “አንጻራዊ ሰላም” መስተዋሉን እና ጅጋ ከተማ “በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር እንደምትገኝ” ተናግረዋል። ሆኖም በጅጋ መስመር እንደ “ወንጌ እና ዴፖ ያሉ ስፍራዎች በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር” መሆናቸውን አመልክተዋል።

በተጨማሪም አከባቢው በተደጋጋሚ ግጭቶችን እያስተናገደ መሆኑን ጠቅሰው ነዋሪው በከፍተኛ ስጋት ኑሮውን ለመግፋት ተገዷል ብለዋል።

በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ በሚገኘው ግጭት በሰዎች እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል። በክልሉ በተደጋጋሚ ግጭት ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች መካክለ አንዱ በሆነው ምዕራብ ጎጃም ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ላይ በርካታ ንጹሃን ሰዎች ህይወት አልፏል።

በቅርቡ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ሸባ በተሰኘች ቀበሌ በእርሻ አውድማ ላይ የነበሩ 11 ሰዎች  “በመንግሥት የጸጥታ አካላት” መገደላቸውን  አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል

ህዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም በዞኑ ደጋ ዳሞት ወረዳ ፈረስ ቤት ከተማ “በፋኖ ታጣቂዎች” ለሁለት ወር ታግተው ከነበሩ 97 አመራሮች መካከል 37 የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮች ተገድለዋል

ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም አቸፈር ወረዳ ዱርቤቴ ከተማ በተፈጸሙ የድሮን ቃቶች ታጣቂዎችን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋልአስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button