ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: 'በፋኖ ታጣቂዎች' ለሁለት ወር ታግተው ከነበሩ 97 አመራሮች መካከል 37ቱ መገደላቸው ተገለጸ 

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1/2017 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ ፈረስ ቤት ከተማ “በፋኖ ታጣቂዎች” ለሁለት ወር ታግተው ከነበሩ 97 አመራሮች መካከል 37 የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአከባቢው ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት ግድያው ህዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም መፈጸሙን ገልጸው ድርጊቱን የ”ፋኖ ታጣቂዎች” እንደፈፀሙት ተናግረዋል።

“ከሁለት ወራት በፊት ከተማው ውስጥ ከባድ ውጊያ ተካሂዶ ነበር። ውጊያው እያየለ ሲመጣ መከላከያ ሠራዊቱ ለመሸሽ ተገደደ። ያን ጊዜ አመራሮቹ ብቻቸውን ቀሩ” ሲሉ የገለጹት ነዋሪው አክለውም የ”ፋኖ ታጣቂዎች” ወዲያውኑ ከተማዋ ውስጥ በመግባት አመራሮቹን መያዛቸውን ተናግረዋል።

“አመራሮቹ ሀገር ሰላም ብለው ተኝተው ጠዋት ሲነሱ የመንግስት ኃይሎች የሉም። የዚያን ዕለት መጀመሪያ የወረዳውን ዋና አስተዳዳሪውን ነው ታጣቂዎቹ የያዟቸው ከዛም ህዝብ መሃል ጫማ አስወልቀው እየጨፈሩ በህዝብ ፊት ሲያዞሯቸው ነበር” ሲሉ የገለጹት ነዋሪው አያይዘውም ከዋና አስተዳዳሪው በተጨማሪ ሌሎች 97 የሚደርሱ አመራሮች፣ የቀበሌ ሊቀመንበሮች እንዲሁም የሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ሃላፊዎችን ይዘው መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

ከሁለት ወራት እስር በኋላም ባሳለፍነው ሳምንት አርብ ህዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም የፋኖ ታጣቂዎች ከመንግሥት የጸጥታ አካላት ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ አመራሮቹ እንደተገደሉ ገልጸዋል።

“ሁለት ወራት በእስር አቆይተዋቸው ባለፈው ከመከላከያ ጋር ግጭት ውስጥ ሲገቡ ከያዟቸው መካከል የተወሰኑትን ገደሏቸው። የተገደሉትም ፈረስ ቤት ሚካኤል በሚባል አቅራቢያ ቅዳሜ ገበያ የሚባል ሳምንታዊ ገበያ የሚውልበት ቦታ ነው” ብለዋል።

ሌላኛው ታከለ ተሾመ (ስማቸው የተቀየረ) የተባሉት የአከባቢው ነዋሪ በበኩላቸው የአመራሮቹን ግድያ ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“መስከረም ወር ላይ ነው ፋኖ ከተማዋን ሲይዝ አመራሮቹም ተይዘው የተወሰዱት። ከመቶ በላይ ናቸው ተወስደው የነበሩት” ያሉት ታከለ አክለውም እሳቸው የሚያውቋቸው ከ20 በላይ የሚሆኑ የስራ ሃላፊዎች ባለፈው ሳምንት መገደላቸውን ተናግረዋል።

“ከተያዙት ውስጥ ነጻ ትሆናላችሁ ክፈሉ ተብለው እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ከፍለው የተለቀቁ እንዳሉ አውቃለሁ። በተለይ ከተማው ውስጥ የሚሰሩ የቀበሌ ሊቀመንበሮች። አሁን የተገደሉት ከተያዙት መካከል የተወሰኑት ናቸው። እኔ እንኳን በግሌ በሰፈር በማህበራዊ ህይወት የማውቃቸው ከ20 በላይ ናቸው የተገደሉት” ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።

በተጨምሪም ቀብራቸው በተገደሉበት ዕለት ቅዳሜ በከተማዋ በሚገኙ ገብርኤል እና ጠጠር ድንጋይ መድኃኔአለም ቤተክርስቲያን መፈጸሙን ጠቁመዋል።

አያይዘውም አሁን ላይ ከተማዋ በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር መሆኗን ጠቅሰው ነገር ግን ነዋሪዎች በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው በወቅታዊ የሰላም እና የጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ህዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ “ጽንፈኛው ቡድን በፈረስ ቤት 37 ወገኖችን በግፍ ጨፍጭፏል” ሲሉ ገልጸዋል።

ሃላፊው “ጽንፈኛ” ሲሉ የጠሯቸው ሃይሎች በምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ ፈረስ ቤት ሚካኤል በሚባል ሥፍራ የሕዝብ እና የመንግሥት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ 97 ሰዎችን ከመስከረም 29/2017 ዓ.ም ጀምሮ አስረው ማቆየታቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም ኅዳር 27/2017 ዓ.ም “37 ወገኖች በግፍ ተጨፍጭፈዋል” ብለዋል።

አክለውም “የተፈጸመው ድርጊት ከአማራ ሕዝብ ታሪክ ያፈነገጠ እና ነውር ነው” ሲሉ ተችተዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳደር ግድያውን አስመልክቶ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ “ጽንፈኛ” ሲል የገለጻቸው ኃይሎች ከ90 በላይ የሚኾኑ ንጹሐንን ከመስከረም 29/2017 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ካቆዩ በኋላ ከእያንዳንዳቸው እስከ አንድ ሚሊየን ብር የሚደርስ ገንዘብ መቀበላቸውን አመልክቷል።

አክሎም “ኅዳር 26/2017 ዓ.ም  ከሌሊቱ 6:00 ሰዓት ላይ በሀገር መከላከያ ሠራዊቱ የደረሰባቸውን ምት መቋቋም ሲያቅታቸው ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ 37 ንጹሐንን በጅምላ ጨፍጭፏል” ብሏል።

በአማራ ክልል በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ በሚገኘው ውጊያ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች ላይ ተመሳሳይ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በቅርቡ በሰሜን ወሎ ዞን የቆቦ ከተማ የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደርቤ በለጠ ህዳር 1 ቀን 2017 ዓ.ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት አከባቢ ቆቦ ከተማ በሚገኘው ሚኪኤሌ ሰለሞን ሆቴል ቁርስ እየተመገቡ ባለበት ወቅት በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል

በተጨማሪም የሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ አስተዳደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት ወ/ሮ ሚሊሹ በቀለ ግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም በታጠቁ ሰዎች ተገድለዋል

በተመሳሳይ መልኩ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በዞኑ የሚገኘው ኤፍራታ ግድም ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ አልብስ አደፍራሽ በአከባቢው በሚንቀሳቀሱ ሀይሎች መገደላቸው ይታወሳልአስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button