ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: የታገዱት የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ህልውናችን አደጋ ላይ ወድቋል ሲሉ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1/2017 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እገዳ ከተጣለባቸው የሲቪክ ድርጅቶች ህልውናችን አደጋ ላይ ወድቋል ሲሉ አስታወቁ፤ የባንክ ሂሳባችን በመታገዱ ለሠራተኞች ደሞዝ መክፈል አልቻልንም ብለዋል።

የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) እና የሕግ ባለሞያዎች ለሰብአዊ መብቶች የተባሉ ሁለቱ የሲቪል ማኅበራት ድርጅት መሪዎች የባንክ ሂሳባቸው በመታገዱ ምክኒያት፣ ለሠራተኞች ደሞዝ መክፈልን ጨምሮ ምንም ዐይነት እንቅስቃሴ ማድረግ ባለመቻላቸው ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ገልጸዋል።

የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ዳይሬክተር ዶ/ር ሞገስ ደምሴ ማዕከሉ የስራ እንቅስቃሴ በመቋረጡ ለተፈጠሩባቸው ችግሮች መፍትሔ ማግኘት አለመቻላቸውን ለቪኦኤ ገልጸዋል።

“የተከሰስንበትን ጉዳይ ተጨማሪ ጉዳዮችን እናጣራለን፣ ሞኒተሪንግ ቡድን እንልካለን ብለው ቡድኑን ከላኩ በኋላ ባሉት ሁለት ሶስት ቀናት ውስጥ አንዳንድ ጉዳዮችን መፍታት የሚያስችሉ በተለይም የሰራተኛ ደመወዝ፣ እና የአስተዳደራዊ ወጪዎችን የመሳሰሉ ጉዳዮችን በአጭሩ እንፈታለን፣ ሌሎቹን ደግሞ እያየን እንፈታለን የሚል ተስፋ ነበር የተሰጠን” ሲሉ ተናግረዋል።

ነገር ግን የሞኒተሪንግ ቡድኑ መጥቶ ከሄደ በኋላ ሌላ ምንም አይነት ምላሽ አላገኘንም ሲሉ ሃላፊው ገልጸዋል። “ተደጋጋሚ ጥያቄዎች በደብዳቤ ጭምር አቅርበናል ምላሽ ይሰጡናል ብለን እየጠበቅን ነው” ብለዋል።

ሌላኛው የታገደው ድርጅት የሕግ ባለሞያዎች ለሰብአዊ መብቶች ዋና ዳይሬክተር አቶ አመሃ መኮንን በበኩላቸው የባንክ ሂሳባቸው ከህግ ውጭ እንደታገደባቸው በመግለጽ ደመወዝ መክፈል አልቻልንም፣ ሰራተኞቻችን ችግር ላይ ናቸው ብለዋል።

“በሲቪል ማህበራት ላይ የሚደረግ ምርመራ የድርጅቶቹን የዕለት ተዕለት የስራ እንቅስቃሴ በማያደናቅፍ እና የድርጅቶቹን ህልውና ጥያቄ ውስጥ በማያስገባ መልኩ መከናወን እንዳለበት” ህጉ ይገልጻል ሲሉ አስታውቀዋል።  

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ነገር ግን አሁን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረብን ነው ብለዋል፤ 18 የሚደርሱ ሰራተኞቻችነን ደመወዝ መክፈል አልቻልንም ሲሉ ገልጸዋል።

እግዱ በአፋጣኝ የማይነሳል ከሆነ ህልውናችን አደጋ ላይ ነው ሲሉ ሃላፊዎቹ አመላክተዋል። በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ድርጅቶቹ ያላቸው እጣፈንታ መዘጋት ነው የሚሆነው ሲሉ ጠቁመዋል።

ለሂሳብ እገዳው ባጭር ግዜ እልባት ማግኘት ካልተቻለ ሌሎች ህጋዊ አካሄዶችን በመከተል እግዱን ለማስነሳት እንሰራለን ሲሉ የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ዳይሬክተር ዶ/ር ሞገስ ደምሴ ተደምጠዋል።

ከኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት ቪኦኤ በዘገባው ጠቁሟል።

በተመሳሳይ ዜና በመንግስት ለእግድ የተዳረጉት ሶስቱ ድርጅቶ ከፍተኛውን የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙት ከፈረንሳይ መንግስት የልማት ድርጅት መሆኑን አፍሪካን ኢንተለጀንስ በዘገባው አስታውቋል።

ፈረንሳይ የሲቪል ድርጅቶቹ መታገድ እጅግ እንዳሳሰባትም ዘገባው አመላክቷል።

የፈረንሳይ አለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (AFD) ሶስቱንም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድጋፍ እንደሚያደርግ የጠቆመው ዘገባው በአጠቃላይ አንድ ነጥብ አስራ አምስት ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።

ከሲቪል ድርጅቶቹ በተጨማሪ የፈረንሳይ አለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ ለሲቪል ማህበረስብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከሁለት አመት በፊት 54 ሚሊየነ ብር ድጋፍ ማድረጉን ዘገባው አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በሶስቱ የሲቪል ድርጅቶች ላይ እግድ የጣለው  ከሳምንት በፊት የፈረሰው የፈረንሳይ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን ኖኤል ባሮት በአዲስ አበባ ጉብኝት ከማድረጋቸው ከሁለት ቀናት በፊት መሆኑን ዘገባው ጠቁሟል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበራት ተወካዮች ጋር መወያያታቸውን ዘገባው ጠቁሟል ውይይቱ በዋናነት በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን እና ስጋት እየፈጠረ ባለው ልዩነቶችን ማስተናገድ አዳጋች መሆኑን የተመለከተ እንደነበር አመላክቷል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን “የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)”፣ “የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች” እንዲሁም “ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ” በተባሉት ድርጅቶች ላይ እግድ መጣሉን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።

በተመሳሳይ አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ድርጅቶች በኢትዮጵያ በሰብአዊ መብቶች ላይ በሚሰሩ የሲቪክ ተቋማት ላይ መንግስት የወሰደው የእግድ ውሳኔ የሲቪክ ማህበራትን ምህዳር የሚያጠብ ነው በሚል ትችት ማቅረባቸውን የተመለከቱ ዘገባዎች ቀርበዋል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button