
አዲስ አበባም ታህሳስ 2/ 2017 ዓ/ም፦ በኦርሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሱልልታ ወረዳ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ትናንት ታህሳስ 1/2017 ዓ/ም በፈጸሙት ጥቃት የሱልልታ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ለገሰ ስዩምን ጨምሮ ሁለት ሰዎች ተገደሉ።
ጥቃቱ ሮብ ገበያ በሚባል አካባቢ የተፈጸመ ሲሆን ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውንና ሌሎች ሁለት ሰዎች በታጣቂዎቹ ተይዘው መወሰዳቸውን የወረዳው ኮሚኒኬሽን አስታውቋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎቹ ባደረሱት ጥቃት ከቆሰሉት ሰዎች መካከል የወረዳው የብልጽና ፓርቲ ኃላፊ የሆኑት ሲሳይ በሻዳ እንደሚገኙበት እና ለህክምና ወደ ጫንጮ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተዘግቧል።
ይህ ጥቃት የተፈጸመው በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መገንጠሉን ካስታወቀው በጃል ሰኚ ረጋሳ የሚመራው ቡድን ጋር የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተክትሎ በርካታ የታጠቁ አባላቱ ወደ ተዘጋጁ የስልጠና መዕከላት እየገቡ ባለበት ወቅት ነው።
ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ኃላፊዎች በመንግስት እና የቀድሞ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ማዕከላዊ ዞን አዛዥ ሰኚ ነጋሳ መካከለ የተፈረመውን ስምምነቱን ለማስፈጸም ከማህበረሰቡ ጋር ውይይት ለማድረግ በተሰማሩበት ወቅት መሆኑን የወረዳው ኮሚኒኬሽን ገልጿል።
የሱልልታ ወረዳ በመግለጫው፤ “መንግስት ሽብርተኛው ኦነግ-ሸኔ በሰላማዊ መንገድ እንዲገቡ ጥረት እያደረገ ባለበት ወቅት፤ ከአባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች እና መንግስት ጥሪ ባፈነገጠ መልኩ አሳፋሪ ተግባር ፈጽሟል” ሲል ከሷል።
የኦርሞ ነጻነት ሠራዊት በበኩሉ ትናንት ምሽት ባወታው መግለጫ ጥቃቱን መፈጸሙን አምኗል።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በመግለጫው፤ በፓትሮል ተሽከርካሪ ላይ በነጣጠረ “ኦፕሬሽን” ኮማንደር ለገሰ ስዩም መገደሉን እና የሱልልታ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ ሲሳይ በሻዳ ማቁሰሉን ገልጿል። በተጨማሪም የመከላከያ ሠራዊት እና ፖሊስ አባላትን መግደሉን እና ማገቱን አስታውቋል።
ይህን እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ስታንዳርድ የሰሜን ሸዋ ዞን እና የሱልልታ ወረዳ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ ሀሳባቸውን ማካተት አልተቻለም።
ይህ ግድያ በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና በመንግስት የጸጥታ አካላት መካከል ለስድስት አመታት በዘለቀው ግጭት ምክንያት በመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ላይ ያነጣጠረው ተከታታይ ግድያ አካል ነው።
ከዚህ ቀደም በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም በመንግስት የጸጥታ አካላት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች መካከል ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት የወጫሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ ኮሩን ጨምሮ ከ45 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም የሰሜን ሸዋ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አቶ ንጉሴ የጸጥታውን ሁኔታ ለመከታተል ወደ ካራ አካባቢ ሲጓዙ በጥይት ተመተው ተገድለዋል።
በሰኔ ወር, 2016 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ሳደን ሶዶ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ በቀለ ካቻ በማንነታቸው ባልታወቁ የታጠቁ ሰዎች ተኩስ መገደላቸው ይታወሳል።
በተመሳሳይ ወር 201 ዓ.ም. በምዕራብ ሸዋ ዞን የአዳ በርጋ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አብዲሳ ቀነኒ፣ በበካቴ ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አካባቢ በታጣቂ ቡድን ተገድለዋል።
በተጨማሪም፣ በመጋቢት 2016 ዓ.ም. በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በምስራቅ ወለጋ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ቦኮንጃ፣ በነቀምቴ ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውጭ “በማንነታቸው ባልታወቁ” ጥቃት ፈጻሚዎች መገደላቸውን የኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት አስታውቋል።
ይህ የትጥቅ ግጭት በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ የሰላማዊ ዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን አስከትሏል። አስ