ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ ኦሮሚያን “ተፈናቃይ የሌለበት” ክልል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ መንግስት ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3/ 2017 ዓ/ም፦  በተያዘው አመት መጨረሻ ላይ ኦሮሚያ ክልልን “ከተፈናቃዮች ነፃ” ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲ ገለጹ።  እስካሁን ወደ 900,000 የሚጠጉ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰዋል ብለዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ይህን የተናገሩት ትናንት በተካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ 4ኛ ዓመት 6ኛ የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት መላሽ ነው።

በክልሉ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች እንደነበሩ የገለፁት አቶ አወሉ፤ እነዚህን ዜጎች ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

“በዚህ አመት ለመጨረሻ ጊዜ ኦሮሚያን ከተፈናቃይ ዜጎች ነፃ ለማድረግ እና ሰዎች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው ሊረዱ ይገባል ብለን እየሰራን ነው። ቢያንስ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ነበር። ነገር ግን አሁን ወደ 900,000 የሚጠጉ ሰዎችን ወደ ቀዬአቸው መልሰናል” ብለዋል።

በተጨማሪም በዚህ አመት መጨረሻ የተፈናቀሉ ዜጎችን በሙሉ ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ እና አስፈላጊውን ድጋፍ በቀዬአቸው ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲ/ ፎቶ፡ ኤፍ ኤም ሲ

“[ተፈናቃዮች] በጅማ ውስጥ አሉ፣ በዋለጋ ሳሲጋ እና ሃሮ ሊሙ ወረዳ ውስጥ አሉ፣ በምስራቅ ባሌም አሉ፣ በቦረና በጎሞሌ ወረዳ ውስጥ አሉ። እነዚህን በመለየት ቀሪዎቹን አካባቢዎች በዚህ አመት መጨረሻ ከተፈናቃይ የፀዱ ለማድረግ እየሰራን ነው” ብለዋል።

በሚቀጥለው አመት ደግሞ እነዚህን ሰዎች ሙሉ በሙሉ ከተረጂነት ነፃ ለማድረግ የክልሉ መንግስት አቅዶ እየሰራ መሆኑን አቶ አወሉ ተናግረዋል። “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በተባለ ፕሮግራም ተፈናቃዮቹን ከተረጂነት ነፃ እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ይሁን እንጂ ሊፈጠሩ የሚችሉ እንደ ረሃብና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በቡሳ ጎኖፋ በኩል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ባሳለፍነው አመት ባወጣው ሪፖርት በኦሮሚያ ክልል በግጭት እና በድርቅ ምክንያት ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን አስታውቋል።

በሪፖርቱ መሰረት አብዛኞቹ ተፈናቃዮች (65 በመቶ) በየአካባቢያቸው በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን 18 በመቶው ደግሞ በድርቅ ምክንያት ተፈናቅለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አዲስ ስታንዳርድ በመጋቢት ወር 2016 ዓ/ም ባወጣው ዘገባ በምዕራብ ኦሮሚያ በመንግስት ጸጥታ ሃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል በተካሄደ ግጭት ሳቢያ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ዘግቧል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button