![](wp-content/uploads/2025/01/Dilla-University-1200x645.jpg)
አዲስ አበባ፣ ጥር 22/2017 ዓ.ም፡- በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሃይማኖታዊ ልብስ የሆነውን ኒቃብ በመልበሳቸው ምክንያት በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ ተከልክለወ የነበሩ አርባ አራት ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ጋር የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ ወደ ትምህርታቸው መመለሳቸውን አሰታወቁ።
ተማሪዎቹ ከሳምንት በላይ ለሚሆን ጊዜ ትምህርት፣ ምግብ እና መኝታ ሳያገኙ በመስጂዶች ውስጥ ተጠልለው መቆየታቸውን አስታውሰው ከዩኒቨርስቲው አስተዳደር ጋር ኒቃብ ለብሰው ትምህርታቸውን ለመከታተል የሚያስችላቸው ስምምነት ሰኞ ጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም በመደረሱ ወደ ትምህርታቸው መመለሳቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
የዲላ ዩኒቨርስቲ ሙስሊም ተማሪዎች ሕብረት ሊቀመንበር የሆኑት ኑረዲን አብደላ ተማሪዎቹ ለ10 ቀናት ያህል በካምፓሱ ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ ተከልክለው እንደነበረ አስረድተዋል።
“ጉዳዩን በውስጥ ለመፍታት ሞክረን ነገር ግን አልተሳካልንም ነበረ” ያሉት ሊቀመንበሩ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መግለጫ ከሰጠ በኋላ የዩኒቨርስቲው አስተዳደር ለውይይት እንደጋበዛቸው ገልጸዋል።
በዚህም ሰኞ ምሽት ከተደረገው ውይይት በኋላ ተማሪዎች በማግስቱ ማክሰኞ ዕለት ጀምሮ ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ተወስኗል ብለዋል።
ትምህርት እና ፈተና ላመለጣቸው ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጦልናል ሲሉ አቶ ኑረዲን ገልጸዋል።
ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረጉ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች በበኩላቸው ማክሰኞ ጠዋት ላይ የተማሪዎቹን ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ አረጋግጠዋል።
ለደህንነቷ ሲባል ስሟን እንዳንጠቅስ የጠየቀች ተማሪ በበኩሏ በዩኒቨርሲቲው ተወካዮች እና በዩኒቨርሲቲው አመራሮች መካከል ከተደረገ ውይይት በኋላ ተማሪዎች ወደ ግቢው እንዲመለሱ እንደተፈቀደላቸው ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጻለች።
ሌላኛዋ ተማሪ በበኩሏ ከዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ውጪ ያሳለፈቻቸውን ቀናቶች “በጣም አስቸጋሪ እና ሥነልቦናዊ ጉዳት ያደረሰ” በማለት ገልፃ ጉዳዩ በመፍታቱ የተሰማትን እፎይታ ገልጻለች።
“ከዩኒቨርስቲው ቅጥር ጊቢ ውጪ ብዙ ቀናት አሳልፈናል፣ ከትምህርታችን ርቀን፣ ለብዙ ወጪዎችም ተዳርገን ነበረ። አሁን ግን ተመልሰን ትምህርታችንን መከታተል ጀምረናል” ብላለች።
አክላም ኒቃብ መልበስ “ለሙስሊም ሴቶች የማንነት ምልክት” እንደሆነ ገልጻ የሃይማኖት ነፃነት እንዲከበር ጥሪ አቅርባለች።
በዲላ ዩኒቨርስቲ የተፈጠረው ክስተት በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ተመሳሳይ ቅሬታዎች በተነሱበት ወቅት የተከሰተ ሲሆን 160 የሚሆኑ ሙስሊም የ12ኛ ክፍል ሴት ተማሪዎች ሂጃባቸውን ለማስወገድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ለብሔራዊ ፈተና ከመመዝገብ እንደተገለሉ መዘገባችን ይታወሳል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ እና ፍርድ ቤት ሴት ሙስሊም ተማሪዎቹ የሃይማኖት ልብስ የመልበስ መብታቸውን የሚያረጋግጡ መመሪያዎች ቢሰጡም በአክሱም ከተማ የሚገኙት ትምህርት ቤቶች እነዚህን ትዕዛዞች አላከበሩም ተብሏል።
በዚህም የአክሱም ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ እንዳይለብሱ የሚከለክለውን መመሪያ በማገድ ያስተላለፈውን ውሳኔ ያልተቀበሉ የትምህርት ቤቶቹ ርዕሳነ መምህራን በፖሊስ ተይዘው እንዲቀርቡ አዟል።
ፍርድ ቤቱ ጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው የእስር ማዘዣ ከ2ኛ እስከ 5ኛ የተጠቀሱ ተከሳሾች “የፍርድ ቤቱን ግልፅና ህጋዊ ሥርዓት ሆን ብለው በመጣስ” የፈጸሙት ድርጊት “የፍርድ ቤቱን ስልጣን የሚያዳክም ነው” በማለት ከሷል። አስ