በአፋር ክልል ከ2,250 በላይ የሚደርሱ ተፈናቃዮች ያለምንም እርዳታ ተቀምጠዋል ተብሏል
አዲስ አበባ፣ ጥር 5/2017 ዓ.ም፡- በአፋር እና በኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የመሬት መንቀጥቀጥ እንቅስቃሴ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት “ሁለት ግለሰቦች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን” የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ (ኦቻ) የመሬት መንቀጥቀጡ በመኖሪያ ቤቶች፣ በጤና ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶች እና መንገዶችን ጨምሮ በመሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጿል።
በመንግሳቱ ድርጅት የተቀናጀ የሰብአዊ ድጋፍ አስተባባሪዎች እንዲሁም አጋር ተቋማት ድጋፍ በተዘጋጀው በዚህ ወቅታዊ ሪፖርት ላይ ሁሉን አቀፍ ሰብአዊ ምላሽ እየተካሄደ ቢሆንም ጉልህ ክፍተቶች መኖራቸው ተመላክቷል።
ሪፖርቱ በአፋር ክልል አዋሽ እና በኦሮሚያ ክልል መተሀራ አከባቢ በመንግስት ይመራሉ ያላቸው የዞን አደጋ ምላሽ አስተባባሪ ማዕከላት ተቋቁመው ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት እና የክላስተር ሰራተኞችን በማካተት ቅንጅታዊ አሰራር መፈጠሩን ጠቁሟል።
ባሳለፍነው ሳምንት 4 ሺ የከሰም ስኳር ፋብሪካ ሰራተኞችን ጨምሮ ከ58 ሺ በላይ ግለሰቦች በገቢራሱ ዞን ዱለሳ እና አዋሽ ፈንታሌ ወረዳዎች በተደጋጋሚ እየተስተዋለ በሚገኘው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ሰብዓዊ እርዳታ እያገኙ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ኦቻ በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሠረት የአደጋ አስተዳደር ኮሚሽን ወደ እነዚህ መጠለያ ጣቢያዎች 16 ምግብ የጫኑ መኪናዎችን መላኩን አመልክቷል፤ በተጨማሪም ከዓለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም እና ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ተጨማሪ ድጋፍ ይጠበቃል ብሏል።
እንዲሁም በአፋር ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ለ6 ሺ 780 ቤተሰቦች የምግብ እርዳታ መድረሱን ገልጾ ይሁን እንጂ 2 ሺ 250 ቤተሰቦች ምንም አይነት ድጋፍ ሳያገኙ ቀርተዋል።” ብሏል።
አዲስ ስታንዳርድ በቅርቡ በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተት ሳቢያ ከ30 በላይ ቤቶች መውደማቸውንና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን መዘገቡ ይታወሳል። አስ