አዲስ አበባ፣ ጥር 3/ 2017 ዓ/ም፦ በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የ12ኛ ክፍል ሙስሊም ተማሪዎች የብሔራዊ ፈተና የኦንላይን ምዝገባ ለማከናወን “ሂጃብ እንዲያወልቁ” መጠየቃቸው ባለመቀበላቸው ትናንት ጥር 2 ቀን የምዝገባ ቀኑ እንዳለፋቸው ገለጹ።
ተማሪዎቹ “ሂጃባቸውን እስካላወለቁ ድረስ ምዝገባቸውን እንዲያጠናቅቁ ትምህርት ቤቶቹ መከልከላቸውን” ገልጸው ይህም የሃይማኖታዊ እምነትን መጣስ ነው ብለዋል።
ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች አንድ ተማሪ፣ “ሃይማኖታችን ስለሚከለክል ለብሔራዊ ፈተና ለመመዝገብ ብለን ሂጃባችንን ማውለው አንችልም። ሃይማኖታዊ ግዴታችንን ከመተላለፍ ይልቅ ትምህርታችንን መተው እንመርጣለን” ስትል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጻለች።
ሌላኛው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአክሱም መምህር የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በአካል ተገኝተው በመመዝገብ የሚችሉበት ጊዜ ባለፈው ሳምንት መጠናቀቁን አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ በትምህርት ቤቶች በኩል የሚደረገው የኦንላይን( በይነመረብ) ምዝገባ ጥር 2 ቀን 10 ሰዓት ላይ በይፋ መጠናቀቁን ገልጸዋል። ለማታ ተማሪዎች ደግሞ ምዝገባ እስከሚቀጥለው ሰኞ ድረስ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን አክሱም ከተማ “በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሂጃብ እንዳይለብሱ” መከልከላቸውን የገለጹ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ድርጊቱ “የትምህርት እና የሀይማኖት ነጻነታችንን ይጋፋል” ሲሉ ተቃውመዋል።
የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፀሐፊ የሆኑት ሃጂ መሀመድ ካህሳይ ክልከላው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ወደ 160 የሚጠጉ ተማሪዎች የብሔራዊ ፈተና ምዝገባ እንዳለፋቸው ነው የተገለጸው።
በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው ትምህርት እንዳይከታተሉ መከልከሉን ተከትሎ የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዛሬ ታህሳስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ “ጥያቄያችን በሦስት ቀናት ውስጥ ምላሽ የማያገኝ ከሆነ ከአማኙ ጋር በመመካከር ቀጣይ ሰላማዊ እርምጃ የምንወስድ ይሆናል” ሲል አስስቧል።
ትግራይ ያለችበት ፖለቲካዊ እና ከባቢያዊ ቀውስ በቂ ነው ያለው መግለጫው ሌላ ሃይማኖትን መሠረት ላደረገ የቀውስ በር መክፈት ክልሉ ከድጡ ወደ ማጡ መክተት ነው ሲል አሳስቧል። አስ