ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና: በመሬት መንቀጥቀጥ ስጋት የተነሳ በከሰም ግድብ አቅራቢያ የሚገኙ ነዋሪዎችን ወደ ሌላ ቦታ የማዘዋወር ሥራ እየተሰራ ነው ተባለ

ግድቡ በሬክተር ስኬል እስከ 7 የሚደርስ የመሬት መንቀጥቀጥን የመቋቋም አቅም አለው ተብሏል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30/2017 ዓ.ም፡- በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በከሰም ግድብ አቅራቢያ የሚኖሩ አርብቶ አደሮችን ወደ ሌላ ቦታ የማዘዋወር ስራ እየተሰራ መሆኑን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታወቁ።

የአርብቶ አደሮቹን ወደ ሌላ ቦታ መዘዋወር ያረጋገጡት የዞኑ የኮማንድ ፖስት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አህመድ ኢብራሂም በአደጋው ​​ለተጎዱ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የከሰም ግድብ አስተዳደር ተወካይ የሆኑት አቶ ቢኒያም ውብሻት ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ ግድቡ ዲዛይንና አቅም ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም ግድቡ የመሬት መንቀጥቀጥን እንዲቋቋም ታስቦ በትላልቅ አለቶች እና አሸዋ የተሰራ በመሆኑ በሬክተር ስኬል እስከ 7 የሚደርስ የመሬት መንቀጥቀጥን የሚቋቋም ግድብ መሆኑን ተናግረዋል።

ግድቡ በ1997 የግንባታ ስራው ተጀምሮለት በ2012 አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የገለፁት አቶ ብንያም ውብሸት፤ በመሬት መንቀጥቀጡ እስካሁን ግድቡ ላይ የደረሰ ምንም አይነት ስጋት አለመኖሩን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም የከሰም ግድብ 500 ሚሊዮን ሜትሪክ ክዩብ ውሃ የሚይዝ ሲሆን 94 ሜትር ቁመት እንዳለው ተጠቁሟል፤ በተጨማሪም ግድቡ በአጠቃላይ ከ20 ሺ ሄክተር በላይ እርሻ የማሰራስ አቅም ያለው ግድብ ስለመሆኑ ተመላክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በቅርቡ የአፋር ክልል እና አካባቢው ተከታታይ የሆኑ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶች እያስተናገደ መሆኑ ይታወሳል።

ከዚህ በፊት ቅዳሜ ታህሣሥ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በአቦምሳ ንዝረቱ አዲስ አበባ ድረስ የተሰማ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 8 የተመዘገበ ከፍ ያለ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የአሜሪካ የጂኦሎጂ ሰርቬይ መረጃ አመልክቷል፡፡

በዛው ቀን ቀደም ብሎ 5 ነጥብ 5 ሬክተር  መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ከአዋሽ በስተሰሜን ምስራቅ 44 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተከስቶ ነበር።

በአፋር ክልል ዱላሳ ወረዳ የሚገኘው የከሰም ስኳር ፋብሪካ በተደጋጋሚ እየተከሰተ በሚገኘው የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ያመለክታሉ፤ በወቅቱ የአፋር ክልል የመንግስት ልማት ድረጅቶች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሀሰን ዳውድ ለመንግሥት መገናኛ ብዙሃን እንዳስታወቁት፣ በአካባቢው በተከሰተው ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችና ተቋማት ላይ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል ብለዋል፡፡

“የመሬት መንቀጥቀጡ አሁንም ቀጥሏል” ያሉት አቶ ሀሰን ነዋሪዎችን ከአካባቢው ወደ የማራቅ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በበኩሉ በመሬት መንቀጥቀጡ በተጎዱ አካባቢዎች ፈጣን ግምገማ ማድረጉን ገልጾ 81ሺህ  የሚጠጉ ሰዎች መጎዳታቸውን አመልክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ደግሞ ከተማዋ ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭነት ያላት በመሆኑ የቅድመ ጥንቃቄ የሚረዱ ጥናቶችን ለማድረግ የባለሙያዎች ግብረ ሃይል ለማደራጀት መስማማቱን አስታውቋል።

አስተዳደሩ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስ፣ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም እንዲሁም ከጂኦሎጂካል ሰርቬይ ከመጡ ምሁራን ጋር  ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች ስለተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ እና ንዝረት እንዲሁም አጠቃላይ ስርጭቱን በተመለከተ ተወያይቷል።

በዚህም የባለሙያዎች ግብረ ሃይል በማደራጀት ተገቢውን ጥንቃቄ ከወዲሁ ለማድረግ እንዲያስችል ለአንዳንድ ቅድመ ጥንቃቄ የሚረዱ ጥናቶችን ለማድረግ በጋራ  ለመስራት መስማማታቸው ተመላክቷል።

በቅርቡ አዲስ ስታንዳርድ በአዋሽ ፈንታሌ በተከሰተው ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ከ30 በላይ ቤቶች መፍረሳቸውንና  በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አጎራባች ወደሆኑ አካባቢዎች እየሸሹ መሆናቸውን መዘገቡ ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button