አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30/ 2017 ዓ/ም፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን በከሬዳ እና ጀሎ ቀበሌ፤ “ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ተሻግረው የመጡ ታጣቂዎች” ትናንት ታህሳስ 29/ 2017 ዓ/ም እና ከትላንት በስቲያ በፈጸሙት ጥቃት ሀሉት አርሶ አደሮች መገደላቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ።
“ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ” ተሻግረው በመጡ ታጣቂዎቹ በተፈጸመ ጥቃት አንታዮ ዞላና እና አድማሱ አሰፋ የተባሉ እርሶ አደሮች ተገድለዋል ሲሉ የሟች ቤተሰብ መሆኑን የገለጹ ምንጭ ገልጸዋል።
አድማሱ አሰፋ የታባሉ አርሶ አደር ከምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ ቡልቶ ጀልዴሳ ቀበሌ በመጡ ታጣቂዎች ትናንት 6፡30 ላይ በኮሬ ዞን ጀሎ ቀበሌ መገደላቸውን አስረድተዋል።
አንታዮ ዞላና ደግሞ ከገላና ወረዳ ሻሞሌ ሺዳ ቀበሌ በመጡ ታጣቂዎች ከትላንት በስቲያ 5፡30 ላይ በኮሬ ዞን ከሬዳ ቀበሌ መገደላቸውን ምንጩ ተናግረዋል።
ሌላኛው ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ነዋሪ ጥቃቶቹ ትናንት እና ከትላንት በስቲያ መፈጸሙን ገልጸው ድርጊቱ አንዳሳዘናቸው ጠቅሰዋል።
“የኮረ ህዝብ ዛሬም በከባድ ሁኔታ ውስጥ ሆኑ የገናን በዓል እያከበረ ይገኛ” ሲሉም አክለው ተናግረዋል።
ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የመጡት ታጣቂዎች “የድንበር ማስፋፋት ዘመቻ” በሚል በግጦሽ መሬት ምክንያት ግጭት መፈጠሩን ነዋሪው ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ ግድያውን ከፈጸሙ በኋላ ከብቶች መዝረፋቸውን ምንጮቹ አክለው ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ተሻግረው ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን የገቡ በተባሉ ታጣቂዎች በአካባቢው ጥቃት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያ አይደለም።
በተያዘው ወር ታህሳስ 13 ቀን 2017 ዓ.ም “ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ተሻግረው የመጡ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች” በኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ ቆሬ ቀበሌ በፈጸሙት ጥቃት በእረኝነት ላይ የነበሩ ሁለት የአከባቢው አርሶ አደሮች “በአሰቃቂ ሁኔታ” መገደላቸውን ነዋሪዎችና ኃላፊዎች ተናግረዋል።
ጥቅምት 4/2017 ዓ/ም በዞኑ ርካ ወረዳ ኬሬዳ ቀበሌ ሸኮ በተባለ መንደር ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ተሻግረው የገቡ ሦስት አርሶ አደሮች በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦችን ዋቢ አድርጎ የደርመን ድምጽ ዘግቧል።
ሟቾቹ ግድያው የተፈጸመባቸው ማለዳ ወደ እርሻ ማሳ በመሄድ ላይ እንዳሉ መሆኑን ከሟቾቹ የአንዱ የቅርብ ዘመድ ነኝ ያሉ አስተያየት ሰጪ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ መልኩ መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም. በኮሬ ዞን ከብቶችን ሲጠብቁ በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ አራት አርሶአደሮች መገደላቸው ይታወሳል። አጋቾቹ በመያዣነት የጠየቁትን 100,000 ብር እና አንድ ካርቶን ሲጋራ ከተቀበሉ በኋላ ግድያውን መፈጸማቸው ተገልጿል።
በዞኑ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በሚፈጽሙት ጥቃት ነዋሪዎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸው በስጋት መሞላቱን እየገለጹ ይገኛል። አስ