አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30/2017 ዓ.ም፡- የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከልን (ካርድ) ጨምሮ በአምስት ሀገር በቀል ሲቪል ማህበረስብ ድርጅቶች ላይ የጣለውን እገዳ በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲነሳ አለም አቀፉ ንቅናቄ ለዲሞክራሲ (World Movement for Democracy) የተሰኘ ተቋም ጠየቀ።
በባለስልጣኑ የታገደው የሲቪል ማህበራቱ የባንክ ሂሳብ እንዲለቀቀ ያሳሰበው ተቋሙ እገዳው መንግስት በሲቪል ማህበራት እና በሰብአዊ መብት ዙሪያ በሚሰሩ ተቋማት ላይ የሚያካሂደው አፈና አካል ነው ሲል ተችቷል።
አለም አቀፉ ንቅናቄ ለዲሞክራሲ (World Movement for Democracy) ትላንት ታህሳስ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “በኢትዮጵያ የሲቪል ማሀበራት ምህዳር እየተዘጋ ነው” ሲል ገልጾ ሁኔታው አሳስቦኛል ብሏል፤ የሲቪል ማሀበራትን ይበልጥ ሊያሰራ የሚችል ሁኔታ እንዲፈጠር እና ማሻሻያዎች እንዲካሄዱ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በተያዘው አመት 2017 ዓ.ም በህዳር እና ታህሳስ ወራት በአምስት ታዋቂ የሲቪል ድርጅቶች ላይ የጣለውን እግድ ተቋሙ በመግለጫው አጉልቶ አሳይቷል።
የሲቪል ማህበረስብ ድርጅቶች ባለስልጣን፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን (EHRDC) “ገለልተኛ ባለመሆን ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ምክንያት ማገዱን መዘገባችን ይታወሳል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በያዝነው ወር ታህሳስ መጀመሪያ ቀናት የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከልን (ካርድ) ጨምሮ በሶስት አገር በቀል ሲቪል ማህበረስብ ድርጅቶች ላይ ጥሎ የነበረውን ዕግድ ማንሳቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ዋቡ በማድረግ በዘገባቸን አስታውቀን ነበር።
ካርድ በድጋሚ ለመታገድ ያደረሰው ምክንያት ቀደም ሲል ተጥሎ የነበረው እገዳ ሲነሳ “የተገለጸለትን የእርምት እርምጃዎች ባለመውሰድ“ እንዲሁም “ለተሰጠው ማስጠንቀቂያ ትኩረት መንፈግ/አለመስጠት” የሚል መሆኑን አስታውቆ እግዱን መኮነኑን በዘገባችን ተካቷል።
በርካታ አለም አቀፍ ተቋማት እና የሀገር ውስጥ ድርጅቶች የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በሲቪል ማህበታሩ ላይ የጣለውን እግድ መተቸታቸው የተመለከዩ ዘገባዎች ማቅረባችን ይታወሳል።
ባለስልጣኑ በኢትዮጵያ በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው በሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ እያሳለፈው ያለው የእግድ ውሳኔ አሳስቦኛል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የተመለከተው ይገኝበታል።
በተመሳሳይ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ህዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ መንግስት በሀገሪቱ በሚንቀሳቀሱ ሶስት የሲቪክ ድርጅቶችን ማገዱ “በሲቪክ ማህበር ምህዳር ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት አጉልቶ ያሳያል” ሲል ማውገዙን፤ መንግስት ውሳኔውን እንዲቀለብስ መጠየቁን የተመለከተ ዘገባም ቀርቧል። አስ