አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14/ 2017 ዓ/ም፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ ቆሬ ቀበሌ ትናንት ታህሳስ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት በእረኝነት ላይ የነበሩ ሁለት የአከባቢው አርሶ አደሮች “በአሰቃቂ ሁኔታ” መገደላቸውን ነዋሪዎችና ኃላፊዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪ ጥቃቱ ትናንት እሁድ ታህሳስ 13 አመሻሽ 11:30 ላይ “ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ተሻግረው የመጡ የሸኔ ታጣቂዎች” ባሏቸው አካላት መፈጸሙን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
ነዋሪ አክለውም በጥቃቱ ከብቶቻቸውን በማገድ ላይ የነበሩ ዩኑሲ ኡስማን እና ቡቹቴ ማስረሻ የተባሉ ሁለት ወጣት አርሶ አደሮች መገደላቸውን ጠቁመዋል።
ግድያውን “እጅግ አሰቃቂ” ሲሉ የገለጹት ነዋሪው፤ “መጀመሪያ በክላሽ ከገደሏቸው በኋላ በቆንጨራ ጨፈጨፏቸው፤ ከሚነገረው በላይ በጣም አስነዋሪ እና አሰቃቂ ድርጊት ነው የተፈጸመው።” ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።
አያይዘውም የሟቾች የቀብር ሥነ-ሥርዓት በዛሬው ዕለት እንደሚፈጸም ገልጸዋል።
በአከባቢው ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ግጭቶች እና ተመሣሣይ ጥቃቶች በተደጋጋሚ እንደሚከሰቱ የገለጹት ነዋሪው “ከምዕራብ ጉጂ ዞን የሚመጡ የሸኔ ታጣቂዎች በአከባቢያው ዘልቀው በመግባት ሰላማዊ ሰዎችን እንደሚገድሉና ይህንንም የሚያደርጉት የአከባቢውን ማህበረሰብ በመንግሥት ላይ እንዲነሣሣ ለማድረግ እና አስተዳደሩን ለመገልበጥ ይሆናል።” ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ሌላኛው ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ ነዋሪ በበኩላቸው ጥቃቱ መፈጸሙን አረጋግጠው ሟቾች በወቅቱ በቆሬ ቀበሌ ልዩ ስሙ ጫፋ እርሻ ማሣ ላይ ከብት በማገድ ላይ ባሉበት ወቅት “ባልታወቁ ታጣቂዎች” በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ተናግረዋል።
ጥቃቱን ተከትሎ ህብረተሰቡ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መግባቱን የገለጹት ነዋሪው “ያልተሰበሰበ የጤፍ እና የአደንጓሬ እህል ለመሰብሰብ ማህበረሰቡ በቡድን በቡድን እየሆነ ራሱን እየጠበቀ ነው” ብለዋል።
በተጨማሪም “በአከባቢው የሚስተዋለውን ተደጋጋሚ ጥቃት ለመከላከል የአከባቢው አስተዳደር ሚሊሻዎችን ቢያሰለጥንም ጥቃቶቹ ማቆሚያ አላገኙም” ሲሉ ተደምጠዋል።
በጎርካ ወረዳ የቆሬ ቀበሌ ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት ደስታዬ ዮሐንስ በዚህ ሳምንት ብቻ 3 ሰላማዊ ሰዎች “ከአዋሳኝ ዞኑ በመጡ የሸኔ ታጣቂዎች” መገደላቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።
ምክትል ሊቀመንበሩ ሁኔታው ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ለወረዳው እንዲሁም ለዞኑ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በተደጋጋሚ ቢገለጽም እስከአሁን መፍትሔ ማግኘት አለመቻሉን አክለው ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በአከባቢው በተደጋጋሚ በሚስተዋለው ጥቃት በሰዎች ላይ ከሚደርሰው ጉዳት በተጨማሪ ከብቶች እና ሌሎችም የእህል ምርቶች እንደሚዘረፉ አመልክተዋል።
ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ተሻግረው የገቡ በተባሉ ታጣቂዎች በአካባቢው ጥቃት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያ አይደለም።
ጥቅምት 4/2017 ዓ/ም በዞኑ ርካ ወረዳ ኬሬዳ ቀበሌ ሸኮ በተባለ መንደር ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ተሻግረው የገቡ ሦስት አርሶ አደሮች በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦችን ዋቢ አድርጎ የደርመን ድምጽ ዘግቧል።
ሟቾቹ ግድያው የተፈጸመባቸው ማለዳ ወደ እርሻ ማሳ በመሄድ ላይ እንዳሉ መሆኑን ከሟቾቹ የአንዱ የቅርብ ዘመድ ነኝ ያሉ አስተያየት ሰጪ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ መልኩ መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም. በኮሬ ዞን ከብቶችን ሲጠብቁ በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ አራት አርሶአደሮች መገደላቸው ይታወሳል። አጋቾቹ በመያዣነት የጠየቁትን 100,000 ብር እና አንድ ካርቶን ሲጋራ ከተቀበሉ በኋላ ግድያውን መፈጸማቸው ተገልጿል።
በዞኑ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በሚፈጽሙት ጥቃት ነዋሪዎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸው በስጋት መሞላቱን እየገለጹ ይገኛል። አስ