አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7/2017 ዓ.ም ፡- የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ባሳለፍነው ሳምንት ታህሳስ 2 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያን እና ሶማሊያ መካከል የተፈረመውን የአንካራን ስምምነት ተከትሎ በጎርጎሮሳውያኒ 2025 የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ ሁለቱን ሀገራት የመጎብኘት እቅድ እንዳላቸው አናዶሉ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።
በምስራቅ ቱርክ በምትገኘው ኤርዙሩም ከተማ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ኤርዶጋን ሀገራቱ ከስምምነት ላይ የተደረሱት “ለሰባት ሰዓታት ከፈጀ ስብሰባ” በኋላ መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም “ለትብብራቸው ምስጋና ይግባውና ስምምነቱን ፈርመን ሥራውን ጨርሰናል” ብለዋል።
አያይዘውም “ፈጣሪ ቢፈቅድ በሚቀጥለው አመት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ ኢትዮጵያን እና ሶማሊያን እንደምጎበኝ ለሁለቱም ገራት መሪዎች ተናግሬያለሁ” ማለታቸው ተጠቁሟል።
በቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን አሸማጋይነት በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ እና በሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ ሞሐመድ ቱርክ አንካራ ላይ የተደረሰው ስምምነት አንዳቸው ለሌላኛቸው ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መከበር ያላቸውን ቁርጠኝነት ያረጋገጡበት ነው ተብሏል።
ስምምነቱ የሶማሊያ ፌዴራላዊ የግዛት አንድነትን ባከበረ መልኩ ኢትዮጵያ የባሕር በር መዳረሻ እንዲኖራትና ከዚህም የምታገኛቸውን ልዩ ልዩ ጠቀሜታዎችን እውቅና የሰጠ መሆኑ ተመላክቷል። በተጨማሪም መሪዎቹ ልዩነቶቻቸውን እና አከራካሪ የሆኑ ጉዳዮችን ለመተው መስማማታቸው ተገልጿል።
ኤርዶጋን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ያላቸውን “ልዩ ግንኙነት” ጠቅሰው “ውይይቱን አመቻችተዋል” ብለዋል።
አክለውም “በሶማሊያ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ተሰማርተናል። ከዚህ ጎን ለጎን በአከባቢው የሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎች ላይ እርምጃ ወስደናል። የአንካራው ስምምነት ለኢትዮጵያ በኢኮኖሚው እና በመከላከያው ረገድ የምንችለውን ሁሉ ድጋፍ ያበረክታል ብለዋል።
ሁለቱ ሃገራት በስምምነቱ መሰረት በአራት ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ የቴክኒካል ድርድር ከጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 2025 በፊት ለመጀመር አቅደዋል።
በስምምነቱ መሰረት “ሶማሊያ በአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለከፈሉት መስዋዕትነት እውቅና ሰጥታለች” መባሉ ይታወሳል።
በተጨማሪም የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ውይይቱን የማቀላጠፍ ሚናቸውም እውቅና የተሰጠው ሲሆን ሁለቱ መሪዎች ለቃል ኪዳኑ ተግባራዊ መደረግ እና ወደፊት የሚነሱ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት የቱርክን ቀጣይ ድጋፍ በደስታ ተቀብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የባሕር በር ስምምነት ተከትሎ በቀጠናው ላይ የተፈጠረው ውጥረት ተባብሶ እንደነበረ ይታወሳል። ይህ እርምጃ በሞቃዲሾ በኩል “የሶማሊያን የግዛት ሉዓላዊነት መጣስ” ተደርጎ ተወስዷል። ይህም አለመግባባቱን የበለጠ አክካሮት መቆየቱ ይታወሳል።
ስምምነቱ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ መረጋጋትን እና ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ለማምጣት ወሳኝ እርምጃ ተደርጎ በተለያዩ አካላት ተወሰዷል።
በቅርቡም አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አፍሪካ ህብረትን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ሀገሮች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና በሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ መካከል የተፈረመውን የ አንካራ ስምምነት እንደሚደግፉ መግለጻቸው ይታወቃል። አስ