ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በአማራ ክልል "በመንግሥት ተጠርቷል" በተባለ ሰልፍ ላይ በሶስት ከተሞች በተፈጸሙ የቦምብ ጥቃቶች የሰው ህይወት ማለፉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 10/2017 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል “በመንግሥት አስተባባሪነት” ትናንት ታህሳስ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ተካሄድ በተባለ ሰልፍ ላይ በባህርዳር፣ ወልዲያና ደብረ ብርሃን ከተሞች “በተፈጸሙ የቦምብ ጥቃቶች የአንድ ሰው ህይወት ማልፉንና ሰልፈኞች መቁሰላቸውን” የአይን እማኞች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ በክልሉ መዲና ባሕር ዳር ነዋሪ ትላንት የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ “በክልሉ መንግስት አስተባባሪነት” የተካሄደ ነው ሲሉ ገልጸው በከተማዋ የተለያዩ አከባቢዎች “የቦምብ ጥቃቶች መፈጸማቸውን” ገልጸዋል።

እነዚህ የቦምብ ጥቃቶች የተፈጸሙትም በዳግማዊ ምንልክ፣ አፄ ቴዎድሮስ እና በበላይ ዘለቀ ክፍለ ከተሞች ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።  በጥቃቱም ከጠዋት ጀምሮ “ጥሩንባ እየነፋ ነዋሪው ሰልፍ እንዲወጣ ሲያስተባብር የነበረ ግለሰብ መገደሉን” ነዋሪው ገልጸዋል።

ሌላኛው ስማቸው እንዳንጠቅስ የጠየቁ በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ የሚኖሩ የአይን እማኝ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት በተመሳሳይ በወልድያ በተካሄደው ሰልፍ ላይ “ቦንብ መጣሉንና ሰልፈኞች መቁሰላቸውን” ተናግረዋል።

“ጥቃቱ የደረሰው ጠዋት ሶስት ሰዓት አከባቢ 1ኛ ፖሊስ ጣቢያ ተብሎ በሚጠራው ሰፍር ነው። ቦምቡ ሰልፈኞች ላይ ነው የተወረወረው። ሰልፉን ለመበተን በሚል ይመስላል” ያሉት ነዋሪው አክለውም ጥቃት አድራሾቹ አለመታወቃቸውን ጠቁመዋል።

አያይዘውም በጥቃቱ አራት ሰዎች ቆስለው ወደ ወልዲያ አጠቃላይ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በወጣው አጭር መግለጫ፤ የወልዲያ ከተማ ፖሊስ “የፅንፈኛውን ተልዕኮ” ተቀብለው በህዝብ ላይ ቦንብ ለማፈንዳት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ያላቸውን ሁለት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የአይን እማኑ ለአዲስ ስታንዳርድ አክለው እንደገለጹት “ከሰልፉ በኋላ ወደ መቻሬ አከባቢ በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭቶች ተካሄዷል” ብለዋል።

ዛሬ ታህሳስ 10 ጠዋት 2:30 ጀምሮ ደግሞ ወደ ቃሊም መስመር የከባድ መሣሪያ ተኩስ ድምጽ ሲሰማ እንደነበረ እና ውጊያዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ትናንት ታህሳስ 9 ቀን 2017 ዓ.ም “መንግስት ባዘጋጀው” ሲሉ በገለጹት ሰልፍ ላይ “የተኩስ እሩምታዎች” እንደነበሩ ገልጸዋል።

“ደብረ ብርሃን ጠባሴ አካባቢ አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጽ ሰምተናል” ያሉት ነዋሪው የተኩስ እሩምታውን ማን እንደከፈተው እንደማያውቁ ገልጸው ነገር ግን “የፋኖ ታጣቂዎች ሰልፉን በመቃወም የፈፀሙት እንደሆነ የሚገልጹ ወሬዎች እንደሚናፈሱ” አስታውቀዋል።

አክለውም አርሴማ ሰፈር አከባቢ እሳቸው “የቦምብ ፍንዳታ ሊሆን ይችላል” ብለው የገመቱትን “ከባድ የፍንዳታ ድምጽ” መስማታቸውን ተናግረዋል። ሆኖም ስለደረሰው ጉዳት እንደማያውቁ አመልክተዋል።

በተመሳሳይ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወረዳ ትናንት በተካሄደው ሰልፍ ላይ በመንግስት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል መጠነኛ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን አየለ በላቸው(ለደህንነት ሲባል ስማቸው የተቀየረ) የተባሉ የአይን እማኝ ገልጸዋል።

እንደ አይን እማኙ ገለጻ፣ የተኩስ ለውውጡ ለአጭር ጊዜ የቆየ ሲሆን በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አስረድተዋል።

በተጨማሪም “የፋኖ አባላት የመሩት” የተቃውሞ ሰልፎች አርማንያና መዘዞን ጨምሮ በትናንሽ የወረዳው ከተሞች መካሄዳቸውን እማኙ ተናግረዋል።

አዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረጉት እነዚህ ምንጮች ከትናንትናው ሰልፍ አስቀድሞ በነበሩ ቀናቶች “የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮች በልዩ ልዩ መንገዶች ነዋሪው ሰልፍ እንዲወጣ ሲያስተባብሩ እና በአንዳንድ ቦታዎችም ሲያስገድዱ እንደነበረ” መታዘባቸውን አመላክተዋል።

በአማራ ክልል አንዳንድ ከተሞች የተካሄደውን ሰልፍ ተከትሎ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ “ሰላማዊ ሰልፉ ሕዝባችን ምን ያክል ሰላም እንደሚሻ ያሰያበት ነው” ብለዋል። 

አክለውም ሰልፎች እንዳይካሄዱ ለማስፈራራት እና ለማሸበር ጥረቶች እንደነበሩ ጠቁመው “ሕዝቡ ግን ዛቻ እና ማስፈራሪያዎችን በመተው ሰላምን እንደሚፈልግ በነቂስ ወጥቶ አሳይቷል” ሲል ገልጸዋል።

“ዛሬ ሕዝቡ መንግሥትን ብቻ አይደለም የደገፈው፣ የደገፈው ሰላምን ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ አክለውም “ሰልፉ ሕዝብ ከጎናችን ነው እያለ መንግሥትን በኃይል እናስወግዳለን የሚለውን ኃይል ያጋለጠ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ በአማራ ክልል በተለየዩ ከተሞች የተካሄደው ሕዝባዊ ሰልፍ “በስኬት መጠናቀቁን” ትናንት ታህሳስ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ በመግለጫው “የአማራ ክልል ሕዝብ ለዓመታት የተደቀነበትን የሰቆቃ ቀንበር የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ከተሞች ማካሄዱን” አንስቷል፡፡

ለዓመታት ክልሉ “በጽንፈኛ ኃይሎች ምክንያት በሰቆቃ ሕይዎት ውስጥ እንዲጓዝ፣ እንዲዘረፍ፣ እንዲፈናቀል እና እንዲሰደድ መደረጉን” ጠቁሟል፡፡

የክልሉ ሕዝብ የሰላም ካውንስል እስከመወከል የደረሰ “ሰላሜን መልሱልኝ” ጥያቄውን ከጀመረ መሰነባበቱን የገለጸው ፖሊስ፤ ይሁን እንጂ “ጽንፈኛው ኃይል የማኅበረሰብን የሰላም ጥያቄ “ጆሮ ዳባ ልበስ…በማለት ከሰብል ማቃጠል ጅምሮ የክልሉን ሕዝብ ባሕል እና ወግ የማይገልጽ፣ ዘመኑን የማይመጥን እና ጸያፍ ተግባር ፈጸሟል” ሲል ከሷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button