ዜናፖለቲካ

ዜና፡ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ሀገሮች የአንካራን ስምምነት እንደሚደግፉ ገለጹ 

አዲስ አባባ፣ ታህሳስ 4/ 2017፡- የአፍሪካ ህብረት፣ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ሀገሮች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና በሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ መካከል ታህሳስ 2 ቀን 2017 ዓ/ም የተፈረመውን የአንካራ ስምምነት እንደሚደግፉ ገለጹ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ስምምነቱን “ከፍተኛ ኃላፊነት ያለው አስፈላጊ እርምጃ” ሲሉ እንደሚደግፉ ገልጸው፤  “ያለመዘግየት ስምምነቱን እንዲተገብሩ አጥብቀው” እንደሚያበረታቱ አስታውቀዋል። 

የአውሮፓ ህብረት ስምምነቱ “በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ውጥረትን ለማርገብ የጋራ መከባበር እና ውይይት አስፈላጊነትን” እንደሚያንፀባርቅ ገልጿል። ህብረቱ ለሁለቱም ሀገራት “ትብብር፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት” ያለውን ድጋፍ በድጋሚ ገልጿል።

በተመሳሳይ ሁኔታ አሜሪካም ስምምነቱ የጋራ ጥቅሞችን በማጠናከር “የአገራቱ ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ነፃነትና የግዛት አንድነትን” ትብብር የሚያጎለብት” መሆኑን በመግለጽ እንደምትደግፈው አስታውቃለች። “ለጋራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ዘላቂ የሆነ የባህር መዳረሻ ኢትዮጵያ እንዲኖራት የሚያስችሉ ቴክኒካዊ ድርድሮችን” እንደምትጠብቅ ገልጻለች።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ፣ የጋራሃብት እና የልማት ቢሮ ቃል አቀባይ፤ “በአፍሪካ ቀንድ ትብብርን፣ መረጋጋትን፣ ልማትን እና የጋራ ብልጽግናን ለማሳደግ የተወሰደ እርምጃ” ሲል ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስምምነቱን እንደሚደግፉት ገልጿል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በባሕር በር ሳቢያ በመካከላቸው የተፈጠረውን ውዝግብ ለማርገብ ታህሳስ 2/ 2017ዓ/ም በቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን አሸማጋይነት በአንካራ ስምምነት ፈጽመዋል

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በስምምነቱ መሰረትም ሁለቱ መሪዎች ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና እና ቀጣይነት ያለው የባህር በር መዳረሻ  እንዲኖራት የሚያስችል ሲሆን ይህም የሊዝ ውልን ጨምሮ በኮንትራንት እና በሌሎች ሞዳሊቲዎች በሉዓላዊ የሶማሊያ መንግሥት ስልጣን ስር የሚተገበር መሆኑ ተመላክቷል።

የሁለቱ ሃገራት መሪዎች አንዳቸው ለሌላቸው ሉዓላዊነት እና የግዛታ አንድነት መከበር ያላቸውን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ ለአለም አቀፍ ህግ እንዲሁም ለአፍሪካ ህብረት መርሆዎች መከበር ላይ አጽንኦት መስጠታቸው ተመላክቷል።

ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት በአራት ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ የቴክኒካል ድርድር ከጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 2025 በፊት መጀመርን ያካተተ ነው።

በተጨማሪም “ሶማሊያ በአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለከፈሉት መስዋዕትነት እውቅና ሰጥታለች” ተብሏል።

ይህ ስምምነተ የተፈረመው ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት በኋላ በቀጠናው ላይ የተፈጠረው ውጥረት ተከትሎ ነው። ከሶማሊ ላንድ ጋረ የተፈረመው ስምምነት በሞቃዲሾ በኩል “የሶማሊያን የግዛት ሉዓላዊነት መጣስ” ተደርጎ ተወስዷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button