አዲስ አበባ፣ ህዳር 18/ 2017 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል አሽከርካሪዎች ለከፍተኛ የቤንዚን እጥረት መዳረጋቸውን ተከትሎ የክልሉ መንግስት ሳምንታዊ የኮታ አሰራርን ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑ ተነገረ።
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ትናንት ህዳር 18 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የቤንዚን እጥረቱን ለመቅረፍ እና ገበያውን ለማረጋጋት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በዝርዝር አስቀምጧል።
በዚህም 75 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ የቤንዚን አቅርቦት ከሱዳን እንደሚመጣ ጠቅሶ አሁን ላይ በሱዳን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እና እየጨመረ የመጣው ነዳጅን ወደ ጥቁር ገበያ የማሸጋገር እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ተግዳሮቶቹ ተባብሰው እንዲቀጥሉ ማድረጉን አመላክቷል።
ችግሩን ለመቅረፍም የተለያዩ የማስተካከያ እርምጃዎችን መተግበር መጀመሩን ቢሮው አስታውቋል።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ የሆኑት አቶ ፋንታሁን ፈጠነ እንደገለፁት ሁሉም የመንግስት ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ የግል መኪናዎች፣ የሜትር ታክሲዎች እና አውቶብሶች እንደ ነዳጅ የመያዝ አቅማቸው በሳምንት አንድ ጊዜ መሙላት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
“ቤንዚን በሚሞሉበት ወቅትም የአሽከርካሪው ስልክ ቁጥር፣ የታርጋ ቁጥር እና ቀጣዩ የነዳጅ መሙያ ቀን ተመዝግቦ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል” ሲሉ አቶ ፋንታሁን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ችግሩን ለመፍታት ቢሮው ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው በዚህም ባለፈው ሩብ አመት ብቻ 135,507 ሊትር ነዳጅ በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ መያዙን ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙ አሽከርካሪዎች በበኩላቸው ከቤንዚን እጥረት ጋር በተያያዘ እያጋጠሟቸው የሚገኙትን ችግሮች ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ አብራርተዋል።
በባህር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ቶማስ ገብረማርያም ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ነዳጅ ለማግኘት እየተቸገሩ መሆናቸውን ገልጸው “ችግሩ ከህገ ወጥ ተግባራት እና ከጥቁር ገበያ ንግድ ጋር የተያያዘ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
“ቤንዚን ከማደያ ማግኘት በጣም ፈታኝ ሆኗል፤ አንዴ ከሞላህ በኋላ እንደገና ለመቅዳት እስከ አራት ቀናት ድረስ ሊወስድ ይችላል” ብለዋል።
አክለውም አሁን ላይ በከተማዋ በጥቁር ገበያ አንድ ሊትር ቤንዚን እስከ 225 ብር የሚሸጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም “አሽከርካሪዎች ነዳጅ ከማደያ ለመቅዳት በአማራጭ ወረፋውን ለማለፍ ተጨማሪ 1,000 ብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል” ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።
አያይዘውም የቤንዚን እጥረቱ አሽከርካሪዎችን ብዙ ጊዜ ያለስራ እንዲያሳልፉ ማድረጉን ጠቁመዋል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በጎንደር ከተማ የሚኖሩ አሽከርካሪ በበኩላቸው ቤንዚን ከማደያዎች ማግኘት በጣም አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
አሁን ላይ በከተማዋ አንድ ሊትር ቤንዚን በጥቁር ገበያ እስከ 200 ብር እየተገዛ መሆኑንም ጠቁመዋል።
“ቤንዚን ከማደያ ለመቅዳት ረጅም ሰልፍ መጠበቅ አለብህ። ያም ሆኖ አልቋል ተብለህ ልትመለስ ትችላለህ” ብለዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው።
አቶ አንተነው አየለ (ስማቸው ለደህንነታቸው ሲባል የተቀየረ) የነዳጅ እጥረቱ በትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳደሩን ይገልጻሉ።
“ከሳምንት በፊት ለአጭር ርቀት ጉዞ 10 ብር የሚያስከፍሉት ባለሶስት ጎማ ተሽከርካሪዎች በአሁኑ ሰዓት 15 ብር እያስከፈሉ ይገኛል” ያሉት አቶ አንተነው አክለውም “ይህ የሆነበት ምክንያት በከተማዋ ውስጥ ያለው የቤንዚን አቅርቦት በጣም ትንሽ ስለሆነ ነው” ብለዋል።
የከባድ ጭነት መኪና ባለቤት የሆኑት አቶ አንተነው በነዳጅ እጥረት ምክንያት ስራቸውን ለማቆም መገደዳቸውንም አክለው ገልጸዋል።
በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት አንድ ሊትር ቤንዚን 200 ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በሃገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች የተከሰተው የቤንዚን እጥረት እና የነዳጅ ጥቁር ገበያ መስፋፋት አሽከርካሪዎችንና ነዋሪዎችን ለከፍተኛ ችግር እየዳረገ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም በሲዳማ ክልል ርዕሰ ከተማ በሆነችው ሀዋሳ የቤንዚን እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ እንደሚገኝ እና ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ መሆናቸውን አሽከርካሪዎችን በማናገር መዘገባችን ይታወሳል።
በወቅቱ ጉዳዩን በተመለከተ ከኢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሲዳማ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ ቡርቃ ቡጡላ ችግሩ ማጋጠሙን አምነው የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ከሚመለከተው የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ህገ-ወጥነትን በተመለከተም የክልሉ ንግድ ቢሮ ከሃዋሳ ከተማ አስተዳደር እና ከሚመለከታቸው የፖሊስ ኮሚሽን አካላት ጋር በመቀናጀት ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ ቤንዚን በማታ እንዳይሸጥ መከልከሉን ገልጸዋል።
የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስትሩ ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው በትናንትናው ዕለት ከነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ለችግሮቹ የነዳጅ ኩባንያዎች በዋናነት ኃላፊነት እንደሚወስዱ አጽንኦት በመስጠት “ህግ እና አሰራር የሚጥሱ ኩባንያዎች ከባድ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። አስ