ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ 'ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መነጠሉን' ይፋ ካደረገው ማዕከላዊ ዞን ዕዝ ጋር መንግስት ለመወያየት ዘግጁ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1/ 2017 ዓ/ም፦ በቅርቡ ‘በጃል መሮ ከሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቡድን መነጠሉን’ ይፋ ካደረገው ከማዕከላዊ ዞን ዕዝ ጋር፤ መንግስት የሰላም ውይይት በማድረግ ልዩነትን ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።

የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ትላንት በማህበራዊ ትስስረ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከዚህ ቀደም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ማዕከላዊ ዞን ዕዝ “ከመንግስት ጋር የሰላም ውይይት ለማድረግ ያሳየውን ፍላጎት መንግስት በዕጅጉ የሚያበረታታውና በበጎ አይን የሚመለከተው ” መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት ይህን ያለው፤ በጃል ሰኚ ነጋሳ የሚመራው የማዕከላዊ ዞን ዕዝ፤ በጃል መሮ ወይም ኩምሳ ዲሪባ ከሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መገልጠሉን ማስታወቁን ተከትሎ ነው።

የድርጅቱ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የማዕከላዊ ዞን የቀድሞ አዛዥ ጃል ሰኚ ነጋሳ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ እሳቸው የሚመሩት ቡድን በጃል መሮ ወይም ኩምሳ ዲሪባ ከሚመራው በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ድርጅት መነጠሉን ጠቅሰው ድርጅቱ “መተዳደሪያ ህግ እና ደንብ” የሌለው ነው ሲሉም ተችተዋል። መሪውን ጃል መሮን “አምባገነን” ሲሉ ጠርተዋል።

በዚህም ምክንያት “በተለያዩ አካባቢዎች ውጊያ እያደረጉ የሚገኙት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ኃይሎች ወደ ስርዓት አልበኝነት ተሸጋግሯል” ሲሉ ገልጸዋል።

በኦሮሚያ የቀጠለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ነን ሲሉም ጃል ሰኚ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ህዝብ ግንኙነት ፅህፈት ቤት፤ ሰኚ ነጋሳ ከወራት በፊት ከቡድኑ “በክህደት ተግባር” መባረራቸውን ገልጿል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ትላንት ባሰፈሩት ጽሁፋቸው፤ “ቡድኑ {በጃል ሰኚ የሚመራው ማዕከላዊ ዞን ዕዝ} ፍላጎቱን በተግባር ለማሳየት ቁርጠኝነት ካለው፤ መንግስት ቃል በገባው መሰረት ረጅም መንገድ ሄዶ በመቀበል ለሰላም ውይይት ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል” ብለዋል።    

መንግስት ሰላማዊ መንገድ እና የእርቅ መንገድን በመምረጥ እየገቡ ላሉ እና ለመግባት እያሰቡ ላሉ ታጣቂዎች “ እንዲቋቋሙ እና ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን በሙሉ ማመቻቸት አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን” ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም “መንግስት የሃሳብ ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማራመድ ለሚሹ አካላት ለሃሳብ ክርክር የሚመች የፖለቲካ ምህዳር የሚያመቻች መሆኑን” አረጋግጠዋል። 

የማዕከላዊ ዞን ዕዝ ያሳየውን የሰላም ንግግር ፍላጎት የክልሉ መንግስት የሚያበረታታው እና ለሰኬታማነቱ የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን በሙሉ በመፍጠር ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ለፍታት ዝግዱ ነው ሲሉ የገለጹት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ ሁሉም ባለድርሻ አክላላት የታየው የሰላም ፍላጎት እንዲሳካ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። 

በጃል ሰኚ ነጋሳ የሚመራው የማዕከላዊ ዞን ዕዝ በጃል መሮ ከሚመራው የኦሮሚ ነጻነት ሠራዊት መነጠሉን ማስታወቁን ተከትሎ ቡድኑ የውስጥ ክፍፍል አልተፈጠረም ሲል አስተባብሏል

ባሳለፍነው ሳምንት ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረገው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ህዝብ ግንኙነት ፅህፈት ቤት፤ ሰኚ ነጋሳ “ከመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚጠቁሙ ማስረጃዎች መኖራቸውን” በመግለጽ ከወራት በፊት ከቡድኑ “በክህደት ተግባር” ተባረዋል ብሏል። 

“በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ውስጥ ምንም ክፍፍል የለም፣ በትንሹም ቢሆን። ሰኚ የቀድሞ የድርጅቱ አባል ሲሆን ድርጊቱም በመላው ኦሮሚያ በሚገኙ በሁሉም የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አዛዦች የተወገዘ ነው” ሲል ጽህፈት ቤቱ አክሎ መግለጹን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ ይታወቃል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button