ዜናፖለቲካ

ዜና: “ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስራውን እንዳይሰራ ሲደረግ የነበረው እንቅስቃሴ አሁን ላይ ወደ ከፋ ደረጃ ተሸጋግሯል” - አቶ ጌታቸው ረዳ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 16/2017 ዓ.ም፡- የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ አስመለክተው ለጋዜጠኞች ትላንት ህዳር 15 ቀን 2017 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ “የትግራይን ፖለቲካ ወደ ተባባሰ ችግር እየገባ ይገኛል” ሲሉ ገልጸዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስራውን እንዳይሰራ ሲደረግ የነበረው እንቅስቃሴ አሁን ላይ ወደ ከፋ ደረጃ ተሸጋግሯል ሲሉ የገለጹት አቶ ጌታቸው በዞኖችና በወረዳው ህገወጥ አሰራር እየተሰራ ነው ብለዋል።

አቶ ጌታቸው በጋዜጣዊ መግለጫቸው በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ችግር በክልሉ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ህይወት ላይ ከፍተኛ ጫና እና ስጋት መፍጠሩን አስታውቀዋል።

የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ከግምት ውስጥ ያላስገባ የስልጣን ወንበር ላይ ብቻ የተመረኮዘ ውጥረት የወለደው ግጭትና ትርምስ እየተፈጠረ ነው ብለዋል።

“ጉባኤ ያካሄደው ቡድን ከዞን እስከ ቀበሌ ባለው ኔትዎርክ አማካኝነት የመንግስት ስራ እንዲሽመደድ በማድረግ መፈንቅለ መንግስት እየፈጸመ ይገኛል” ሲሉም ተችተዋል።

“ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ የቆየው ሃይል” ሲሉ የገለጹት ቡድን ሁሉንም ነገር አፍኖ ወደ ስልጣን ለመመለስ እየሰራ ነው ብለዋል።

“ሙሉ ትኩረታችንን የተፈናቀሉ ዜጎችን መመለስ፣ የትግራይን ደህንነት ማረጋገጥ ይሆናል ብለን ያስቀመጥነውን ተግባር ትተን ወደ ሌላ የስልጣን ሽኩቻ እንድንገባ ተገድደናል” ሲሉ ተደምጠዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“ከዚህ ቀደም የስልጣን ሞኖፖሊ ይዞ የነበረው ሀይል በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ስለተሸራረፈበት ስልጣኑ ለማስመለስ ብቻ በማሰብ እየተንቀሳቀሰ ነው” ሲሉ ኮንነዋል።

ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አጀንዳዎችን ትቶ “ስልጣኔን ልመልስ እንጂ ሌላውን ከዚያ በኋላ እመለስበታለሁ” በሚል ቡድኑ እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ “ወንበራችንን ተቀምተናል የሚሉ አካላት ስልጣናችንን በጉልበት እናስመልሳለን ወደሚል ውድቀት” ተገብቷል ብለዋል።

ይህም የትግራይን ፖለቲካ ወደ ተባባሰ ችግር እያስገባው ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

“መፈንቅለ መንግስት በወታደሮች ብቻ የሚካሄድ አይደለም” ያሉት አቶ ጌታቸው “ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ በምክር ቤትም ሆነ በሌሎች መዋቅሮች ያለውን መንግስትን ለማፍረስ የሚሞክር ሁሉ መፈንቅለ መንግስት እያደረገ ነው” ብለዋል።

“ከሃላፊነት ተባረሃል፣ ወርደሃል ስለዚህም የስልጣን እና ማህተም አስረክበሃል ማለት መፈንቅለ መንግስት ማካሄድ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የጀመርነው ስራ በተፈጠረው የፖለቲካ ልዩነት ምክንያት ሙሉ ትኩረት ሰጥተን እንዳንሰራ አድርጎናል ሲሉ የተደመጡት ፕሬዝዳንቱ “ይሁን እንጂ ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራችን በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ከቀያቸወ የተፈናቀሉ እና ወደ ጎረቤት ሀገር የተሰደዱ ነዋሪዎችን ለመመለስ ከፌደራል መንግስት ጋር ጥሩ መግባባት ላይ እንገኛለን” ብለዋል።

በትግራይ በተለይም በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በፕሪቶርያው ስምምነት አፈጻጸም ላይ አሉታዊ ተጽእኖው ከፍተኛ ነው። ሙሉ ትኩረታችንን ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው አንዲመለሱ ከማድረግ ይልቅ፣ ሙሉ ትኩረታችን በጸለምት እና ራያ አከባቢ የተመለሱ ተፈናቃዮች ያጋጠማቸውን ችግር ለመፍታት ከማድረግ ይልቅ፣ ወደ ወንበር ይገባኛል ትግል ተገብቷል ሲሉ ገልጸዋል።

በእነ ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የተካሄደው ጉባኤው “በፓርቲው አሰራርም ሆነ የፌዴራል መንግስቱ በሰጠው መመሪያ መሰረት ህጋዊ አይደለም” ያሉት አቶ ጌታቸው፣ እርሳቸውና ባልደረቦቻቸው የተፈጠረውን አለመግባባት በእርቅና በድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን  ተናግረዋል።

“እንደ ህወሓት መዳን ከፈለግን በውስጥ ሃይሎች እንጂ በውጪ ሃይሎች መሆን የለበትም” ሲሉ ገልጸዋል።

“ከልቡ ህወሓትን ለማዳን በሚል ወደ ጉባኤ ከገባው ጋርም ይሁን ከልቡ ህወሓትን ለማዳን በሚል በጉባኤው ካልተገኘው አካል ጋር ለመደራደር ዝግጁነት” መኖሩን አስታውቀዋል።

“በአሁኑ ወቅት የፌደራል መንግስቱ አቋም ችግራችሁን ፈትታችሁ፣ አንድ የምትሆኑበትን መንገድ ፈጥራችሁ መምጣት አለባችሁ የሚል ነው” ሲሉ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

“ሰራዊቱ የትግራይን ህልውና ለማረጋገጥ የቆመ እንጂ የግለሰቦችን የወንበር ጥም ለማረጋገጥ መንቀሳቀስ የለበትም” ሲሉም አሳስበዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button