አዲስ አበባ፣ ህዳር 16 2017 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት እና በፋኖ ሚሊሻዎች ተፈጽሟል የተባለውን ግድያ በተመለከተ በመገናኛ ብዙኃን ቀርበው የተናገሩ 16 ነዋሪዎች በመንግስት ኃይሎች መታሰራቸው ተገለጸ።
ነዋሪዎቹ በአካባቢው ያለው ግጭት እያደረሰባቸውን ያለውን ተፅእኖ በመግለጽ እና ተጠያቂነትን እንዲረጋገጥ በሚዲያ ጥሪ አቅርበዋል። ነዋሪዎቹ የሰጡት አስታየት ቲክቶክ እና ፌስቡክን ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል።
ይህንን ተከትሎ 16 ነዋሪዎች በመንግስት ኃይሎች ለዕስር መዳረጋቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ለደህንነቱ በመስጋት ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የደራ ወረዳ ዋሬ ገብሮ ቀበሌ ነዋሪ በእስር ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከል እናቱ እና የአጎቱ ሚስት እንደሚገኙ ተናግሯል። እናቱ እና የአጎቱ ሚስት ህዳር 13፣ 2017 ዓ/ም መታሰራቸውን ተናግሯል።
የመንግስት ኃይሎችን የከሰሰው ነዋሪው እስሩ የተፈጸመው በአካባቢው ግጭት እየተካሄደ ባለበት ወቅት መሆኑን በመግለጽ የሞቱት ንጹሃን ሰዎች የተገደሉት በፋኖ ሚሊሻ መሆኑን ገልጸዋል።
“የመንግስት ኃይሎች አባቴን እና ወንድሙን ለማሰር ጠዋት ወደ ቤታችን መጡ። ይሁን እንጂ ቤት አልነበሩም ነበር፤ አንዳን ስድቦችን ከተሳደቡ በኋላ እናቴን እና የአጎቴን ሚስት ወስዷቸው” ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል።
አክሎም የታሰሩት ሴቶች በቁጥጥር ስር ቢውሉም በአደባባይም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ምንም አለመናገራቸውን ገልጾ ይልቅ አባቱና አጎቱ ማኅበረሰቡን በመወከል ድምጽ ሲሆኑ ነበር ብሏል።
ምንጩ አክሎም በጨካ ከተማ በሚገኘው ጨካ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ታስረው እንደሚገኙና ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ገልጿል።
ሌላኛው ስሙ እናይጠቀስ የጠየቀ የዋሬ ገብሮ ቀበሌ ነዋሪ፤ ወንድሙ በሚዲያ በመቅረብ ስጋታቸውን መግለጹን ተከትሎ ህዳር 13 ጠዋት 3፡30 ላይ መታሰሩን ገልጿል።
“በጨካ ከተማ በሚገኘው ጨካ የመጀመሪያ ደርጃ ት/ቤት ውስጥ ነው ታስሮ የሚገኘው” ያለው ነዋሪው፤ የወንድሙ ስጋት የአጠቃላይ ማህበረሰቡን የሚያንፀባርቅ እንደነበር ተናግሯል።
ለአዲስ ስታንዳርድ በተላከው የታሳሪዎች ስም ዝርዝር ውስጥ፤ መዝገቡ ተሾመ፣ ታመነ ገራዶ፣ አባዬ አሚኑ፣ አስማረ ተመስገን፣ ካሲዬ መኮንን እና ሙላለም ወርቁ የተባሉ ሰዎች ይገኙበታል። “እስካሁን ድረስ አንዳቸውም ፍርድ ቤት አለቀረቡም” ሲል ነዋሪው ገልጿል።
ነዋሪው እንደገለጸው፤ የመንግስት ኃይሎች በመገናኛ ብዙሃን እና በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በተሰራጨው ቪዲዮ የታዩትን ሰዎች “በህዝብ መካከል ልዩነቶች እንዲስፋፉ መረጃዎችን አሰራጭተዋል” ሲል ከሷል። “ነዋሪዎቹ ግጭት እንዲቆም እና ፍትህ እንረጋገጥ በቻ ነው የጠየቁት። እነዚህ መሰረታዊ መብቶች እንጂ ወንጀሎች አይደሉም” ብሏል።
በእስሩ በተጨማሪ ከፈተኛ የሰዎች መፈናቀል እና የንብረት ውድመት መከሰቱን የገለጸው ነዋሪው፤ “ስለገጠመን ችግር ስንናገር ቆይተናል ነገር ግን ደህንነታችን እና ስጋቶቻችንን ከመፍታት ይልቅ መንግስት እየታሰረን ነው” ብሏል።
ከቅርብ አመታት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የምትገኘው የደራ ወረዳ መንግስት ሃይሎች፣ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረግ የግጭት አውድማ ሆናለች። በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያ በመሰራጨት ላይ ያለው የደራ ወረዳ ነዋሪ የሆነ የ17 አመት ወጣት አንገቱ ሲቆረጥ የሚያሳይ ቪዲዮ በርካቶችን ያሳዘነ፣ ቁጣን የቀሰቀሰ ተግባር ሁኗል።
ዘገባዎች እንዳመላከቱት “በፋኖ ታጣቂዎች” ድርጊቱ የተፈጸመበት ወጣት ደረጀ አማረ የተባለ የደራ ወረዳ ነዋሪ ሲሆን ቪዲዮው አሁን ላይ ቤሰራጭም ድርጊቱ ከተፈጸመ ከሁለት ወራት በላይ አልፎታል።
የኦሮሚያ ከልል መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ “በፋኖ ታጣቂዎች” የ17 አመት ወጣት ላይ ተፈጽሟል የተባለውን አሰቃቂ ድርጊት በተናጠል ባወጡት መግለጫ አወገዘዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት በሰጠው መግለጫ የክልሉ መንግስት “በጽንፈኛ የፋኖ አካላት የተፈጸመውን የጭካኔና አሰቃቁ ድርጉት እንደሚያወግዝ እና የዜጎችን ድህንነት ለማስጠበቅ” የሚሰራ መሆኑን ገልጿል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ “ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግስት ኃይሎች በህዝባችን ላይ እየተፈጸመ ያለው አሰቃቂ ግድያ ከባድ የጦር ወንጀል ነው” ብሏል። ፓርቲው በመግለጫው በተፈጸመው የጭካኔ ግድያ ከፋኖ ታጣቂዎች በተጨማሪ መንግስትን ከሷል። “በግልጽ በቪዲዮ ላይ ከሚታየው በላይ ፋኖ የገለደሏቸው ሰዎች እንዳይቀበሩ መከላከያ ሠራዊት ህዝቡን ከልክሏል” ብሏል መግለጫው።አስ