ቢዝነስዜና

ዜና፡ አስመጪዎች በባንኩ የውሳኔ መዘግየት ምክንያት የውጭ ምንዛሪ መጠቀም አለመቻላቸውን ገለጹ 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5/ 2017 ዓ/ም፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ለአስመጪዎች ከ282 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ መደልደሉን አስታውቋል።  እስከ አሁን ያለዉ አማካይ አጠቃቀምም ግን 28% ብቻ ነዉ ብሏል፡፡

አስመጪዎች በበኩላቸው በባንኩ የውሳኔ መዘግየት ምክንያት የውጭ ምንዛሪ መጠቀም አለመቻላቸውን ገለጹ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው አዲሱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ከገበያ እንዲገዙ የሚያስችል መመሪያ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን አስታውቋል።

ይህ አካሄድም ባንኮች ከደንበኞች ለሚቀርቡላቸው የውጭ ምንዛሪ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡና የውጭ ምንዛሪ ድልድልን ውጤታማነት እንደሚያሻሽል ተገልጿል።

“ባለፉት ሁለት ወራት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጪ ምንዛሪ በተወዳዳሪ ዋጋ ከገበያ እየገዛ ለአስመጪዎች በማቅረብ የገቢና ወጪ ንግድ ሥራዎችን በስፋት ሲያከናውን ቆይቷል” ሲል መግለጫው ያትታል።

ባንኩ ከሐምሌ 22/2016ዓ.ም እስከ መስከረም 30/2017 ዓ.ም ድረስ በአራት ዙር ከ282 ሚሊዮን 459 ሺሕ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለተለያዩ የውጭ ምንዛሬ ፈላጊ ደንበኞች መደልደሉን አስታውቋል፡፡

ኾኖም ባንኩ የምንዛሬ አጠቃቀሙ አዝጋሚ ነው ያለ ሲሆን እስካኹን ያለው የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም 28 በመቶ ብቻ መኾኑን ጠቅሷል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ይሁን እንጂ አስመጪዎች በበኩላቸው በባንኩ የውሳኔ መዘግየት ምክንያት የተፈጠረ ችግር ነው ሲሉ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ አስረድተዋል።

በቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ ማርኬቲንግ ማኔጀር የሆኑት ኢያሱ ነቅዐጥበብ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም ላይ የገጠሟቸውን ተግዳሮቶች አብራርተዋል።

አቶ ኢያሱ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ለደንበኞች መደልደሉን ቢገልጽም፣ ችግሩ ከደንበኞች ጋር ሳይሆን ከባንኩ አዝጋሚ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል።

አክለውም “ባንኩ ባዘዘው መሰረት አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ብናሟላም የተመደበልንን የውጭ ምንዛሪ እስካሁን አልተቀበልንም።” ሲሉ አብራርቷል።

በተጨማሪ “ከባንኩ የምናገኘው ምላሽ ወደ በላይ አካል አስተላልፈናል የሚል ነው።” ሲሉ አቶ ኢያሱ ጠቁመዋል።

አክለውም የክሬዲት ደብዳቤ (LC) መክፈትን በተመለከተ የአሰራር ለውጥ መደረጉን ገልጸዋል።

“ከዚህ ቀደም የውጭ ምንዛሪ ከተፈቀደ በኋላ በ15 ቀናት ውስጥ የክሬዲት ደብዳቤ መከፈት ነበረበት። ነገር ግን አሁን ላይ ይህ ቀነ ገደብ ተወግዷል” ያሉት አቶ ኢያሱ፤ የክሬዲት ደብዳቤ ለመክፈት አስፈላጊ ሰነዶችን አሁንም በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ መሰረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ በበኩላቸው ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ ችግሮቹን ለሁለት ከፍለው ገልጸዋቸዋል።

በመጀመሪያ፣ “የውጭ ምንዛሪው ሙሉ በሙሉ እየተለቀቀ አይደለም” ብለዋል።

በሁለተኛ ደረጃ፣ “የውጭ ምንዛሪ ድልድል በበርካታ ሂደቶች ውስጥ ያልፋል፣ ለእንዱስትሪ በሚመጥን ፍጥነት አይደለም ገንዘቡ የሚለቀቀው። ማንኛውም ኢንዱስትሪ ደግሞ የሚያገኘውን ምንዛሬ ቶሎ ቶሎ እያገላበጠ ነው መስራት የሚፈልገው።” በማለት አስረድተዋል።

አግሮኬሚካል ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ሥራ ላይ ተሳታፊ በሆነ ኩባንያ ውስጥ የማርኬቲንግ ሥራ አስኪያጅ የሆኑ ግለሰብ በበኩላቸው አንዳንድ አስመጪዎች በንግድ ባንኮች የተመደበውን የውጭ ምንዛሪ ለመጠቀም የሚያቅማሙበትን ምክንያት ለአዲስ ስታንዳርድ አስረድተዋል።

የመጀመሪያው አስመጪዎች የውጭ ምንዛሪው በሚፈቀድበት ቀን ሳይሆን ክፍያ በሚፈጸምበት ቀን የውጭ ምንዛሪውን መግዛት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰዋል።

ይህም አስመጪዎችን ለከፍተኛ ወጪ እንደሚዳርጋቸው ጠቁመዋል።

ሥራ አስኪያጁ አክለውም ከመጀመሪያው ትእዛዝ እስከ መጨረሻው ክፍያ ድረስ ቢያንስ ሁለት ወራት ሊያልፍ እንደሚችል አመልክተዋል።

ሥለሆነም “በሁለት ወራት ውስጥ ይፋ በሆነው የምንዛሪ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ የሚታይ ከሆነ፣ ግብይት ከማከናወን በፊት ዋጋው እስኪረጋጋ ድረስ መጠበቁ ጥሩ ይሆናል።” ብለዋል።

መንግስት ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ማሳወቁ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንዱን የአሜሪካ ዶላር ይገበያይ ከነበረበት ከ57 ብር በጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም በአማካይ ወደ 125 ብር ከፍ ብሏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button