ቢዝነስዜና

ዜና: በኢትዮጵያ የባቡር አገልግሎትን ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ለማድረግ የሚያስችል ጥናት መጠናቀቁ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4/2017 ዓ.ም፡- ከመንግስታዊው የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን በተጨማሪ በሀገሪቱ የባቡር አገልግሎት ላይ የውጭ ባለሃብቶች እንዲሳተፉበት ለማስቻል ያለመ ጥናት መጠናቀቁ ተገለጸ።

በአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ድጋፍ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ያስጠናው ጥናት በዋናነት በኢትዮጵያ አጠቃላይ የባቡር አገልግሎት ላይ ማሻሻል ያለመ መሆኑን አፍሪካን ኢንተለጀንስ ባስነበበው ዘገባ ጠቁሟል።

ሚኒስቴሩ ያቋቋመው አጥኚ ቡድን ጥናቱን አጠናቆ ከአንድ ወር በፊት ለሚኒስትሩ ማስረከቡን ያመላከተው ዘገባው መንግስታዊውን የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽንን የሚፎካከሩ የግል የባቡር አገልግሎቶች እንዲቋቋሙ መፍቀድ የሚያስችል እቅድ በጥናቱ መካተቱን አስታውቋል።  

ለዚህም ሲባል የባቡር አገልግሎትን የሚፈቅድ፣ የሚቆጣጠር እና የሚያስተባብር ተቋም በባለስልጣን ደረጃ እንዲቋቋም ምክረ ሃሳብ መቅረቡን አመላክቷል።

በጥናቱ ላይ የባቡር አገልግሎት ባለስልጣን ለግል የባቡር አገልግሎቶች ፈቀድ መስጠትን ጨምሮ የባቡር ኔትወርኮችን፣ ጣብያዎችን፣ የጥገና ማዕከላት ለማቋቋም ፍላጎት ላላቸው ባለሃብቶች ፍቃድ የመስጠት ስልጣን እንዲኖረው የሚል በጥናቱ ላይ ምክረ ሀሳብ መቅረቡን ዘገባው ጠቁሟል፤ አዳዲስ የባቡር መስመሮችን እና የትስስር ስራዎችንም መፍቀድ ያካትታል ብሏል።

አሁን ላይ የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን ከአቅሙ እጅግ ባነሰ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ያመላከተው የአፍሪካን ኢንተለጀንስ ዘገባ ለጭነት አገልግሎት ከሚጠቀመባቸው 32 የጭነት ፍርጎዎች ውስጥ በስራ ላይ የሚገኙት 18ቱ ብቻ መሆናቸውን አስታውቋል፤ ለዚህም ዋነኛ ምክንያት የመለዋወጫ እጥረት መሆኑን ጠቁሟል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የባቡር አገልግሎት ዋና ዋና የሎጂስቲክስ ንዑስ ዘርፎችን – ደረቅ ወደብ ፣ ጭነት እና ሎጅስቲክስ አገልግሎቶችን ከመንግስት ብቻ ይዞታነት ነፃ ማድረግ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ በፈረንጆቹ 2026 መጨረሻ ላይ ዝግጁ ይሆናል የሚል የግዜ ሰሌዳ መኖሩን ድረገጹ ለአይኤምኤፍ ከተላከው ሪፖርት መመልከቱን አስታወቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ጥናቱን ለማካሄድ በተቋቋመው ግብረ ሃይል ውስጥ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የተውጣጡ ተወካዮች መካተታቸውን ዘገባው አስታውቋል፤ ከኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን፣ ከኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እና ከኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሃላፊዎች መሳተፋቸውን አመላክቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button