ዜናፖለቲካ

ዜና፡ ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ወደ ተግባር መግባቱን አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምቅ 4/2017 ዓ/ም፦ ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ከትናንት ጥቅምት 3/2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መሆን መጀመሩን አስታውቃለች።

የትብብር ማዕቀፉ ትግበራ መጀመሩ የተገለጸው ጥቅምት 7 ቀን 2017 ዓ.ም.በኡጋንዳ ሊካሄድ ከታቀደው ሁለተኛው የናይል ጉባኤ ቀደም ብሎ ነው።

ለዓመታት ድርድር ሲካሄድበት የቆየው የትብብር ስምምነቱ ተፈጻሚ መሆን የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽንን ለመመስረት ያስችላል ተብሏል።

ኮሚሽኑ የናይል ወንዝን የማስተዳደርና በሁሉም የተፋሰሱ ሃገራት መካከል ፍትሐዊ  አጠቃቀም እንዲኖር ይቆጣጠራል ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ወደ ተፈጻሚነት መግባቱን አስመልክተው በኤክስ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “በአባይ ተፋሰስ ላይ እውነተኛ ትብብር ለመፍጠር ያደረግነው የጋራ ጥረት ታሪካዊ ምዕራፍ ሆኖ ይታወሳል” ብለዋል፡፡ 

አክለውም “ስምምነቱ ወደ ተፈጻሚነት መግባቱ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትን ትስስር ከማጠናከር ባለፈ በጋራ የውሃ ሀብቶች አስተዳደር እና አጠቃቀም ላይ ፍትሃዊነትን ያረጋግጣል” ሲሉ ገልጸዋል።

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው የስምምነቱን አስፈላጊነት አስተጋብተዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ሚኒስትሩ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን “ፍትሃዊና ምክንያታዊ” የናይል ወንዝ ተጠቃሚነትን የሚያበረታታ “የጋራ ህጋዊ ማዕቀፍ” ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።  

በተጨማሪ የትብብር ማዕቀፉ በናይል ወንዝ አጠቃቀም ላይ የሚታየውን ኢ-ፍትሐዊነትን በማስወገድ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።   

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1929 እና ​​በ1959 የተፈረሙትን ለአንድ ወገን ያደሉ እና ግብፅ እና ሱዳንን በናይል ወንዝ ላይ ሰፊ ቁጥጥር እንዲኖራቸው የሚያስችላቸውን የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎችን በመቃወም የተፋሰስ ሃገራቱን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ስትደግፍ ቆይታለች።

እነዚህን ስምምነቶችም የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት፤ ለ”ታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ያደላ ነው” በሚል ተቃውመውታል።

የትብብር ማዕቀፉ ስራ ላይ የዋለዉ ደቡብ ሱዳን በሐምሌ 2016 ዓ.ም. ስምምነቱን ማፅደቋን ተከትሎ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ እና ቡሩንዲ ቀድመው ስምምነቱን አጽድቀዋል።

ግብጽና ሱዳን በበኩላቸው፣ የናይል ተፋሰስ አገራት የትብብር ማዕቀፍ ወደ ትግበራ መግባቱን ተቃውመውታል።

ሁለቱ አገራት፣ የትብብር ማዕቀፉ “ህጋዊ መሠረት የሌለውና “ እና “የዓለማቀፍ ሕጎችን የሚቃረን” ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ማዕቀፉ “በቂ መግባባት” ሳይደረስበት ተዘጋጅቷል ሲሉ ለናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ (እ.ኤ.አ የ1959ኙ) ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል። 

ከዚህ ቀደም የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በመጪው የናይል ተፋሰስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፣ ጉባኤው የናይል ተፋሰስ ሃገራት የትብብር ማዕቀፍን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እና በከባቢው ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም አቅጣጫዎችን ለመዘርጋት ታሪካዊ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል ብለዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button