አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 22/2017 ዓ.ም፡- በሀገሪቱ በርካታ አከባቢዎች በነዳጅ ግብይት ስርዓት የሚስተዋሉ ህገ ወጥ ድርጊቶች እየተባባሱ መምጣታቸው እየተገለጸ ባለበት ወቅት መንግስት ይህንን ህገወጥ ድርጊት ፈጻሚዎች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ ርምጃ እየወሰድኩ ነው ሲል አስታወቀ።
የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ ባለፉት ጥቂት ወራት በተካሄደ የቁጥጥር ስራ በህገወጥ የነዳጅ ግብይት የተሳተፉ 34 የሚሆኑ የነዳጅ ማደያዎች ርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
በተለያዩ አካላት በህገወጥነት ሲዘዋወር የነበረ 385,947.50 ሌትር ነዳጅ በቁጥጥር ስር ዉሎ በህግ አግባብ ተወርሶ ለሽያጭ በማዋል 27,946,712.00 ብር ለመንግስት ገቢ ተደርጓል ሲሉ አስታውቀዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው የነዳጅና ኢነርጅ ባለስልጣን ጋር በመቀናጀት ባለፉት ሁለት ቀናት 54 ማደያዎችን ላይ ቅኝት ማካሄዱን የጠቆሙት ሚንስትሩ 8 የነዳጅ ማደያዎች የተለያዩ የነዳጅ ግብይት ጥሰት ፈፅመዉ በመገኘታቸዉ ለድርጊታቸዉ አስተማሪ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል።
ረጃጅም ሰልፎች በየከተሞች የሚታይበት ሁኔታ የተስተዋለ ቢሆንም በተጨባጭ የቤንዚን አቀርቦት ችግር የለም ያሉት ሚኒስትሩ እጥረት እየተፈጠረ ያለው በህገወጥ ድርጊቶች ነው ሲሉ አመላክተዋል።
በቅኝቱ ተስተውለዋል ብለው ከለዩዋቸው ችግሮች መካከልም ከዲጂታል ግብይት ዉጭ በእጅ በእጅ ክፊያ በመሸጡ፣ አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ነዳጅ በየማደያዉ ዉስጥ እያለ አገልግሎት አለመሰጠቱ፣ በክምችት ካላቸዉ ነዳጅ ቀንሰዉ ለተቆጣጣሪ አካል ሪፖርት መደረጉ የሚሉትን ዘርዝረዋል።
በአዲስ አበባ አንድ ቀን በተደረገ አሰሳ ከ120 ማደያዎች ስድስቱ ብቻ አገልግሎት ሲሰጡ መገኘታቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።
ባሳለፍነው ወር ህዳር መጨረሻ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ቀርበው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ የሥርጭት ችግርን ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቅሰው አክለውም 68 የሚሆኑ ነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ እያላቸው የለም ሲሉ ተገኝተዋልማለታቸውን በዘገባው ተካቷል።
በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ የጥቁር ገበያ የነዳጅ ሽያጭ በመስፋፋ ሳቢያ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ እጥረት እያጋጠማቸው መሆኑን አሽከርካሪዎችን ዋቢ በማድረግ በትላንትናው ዕለት ታህሳስ 21 ቀን መዘገባችን ይታወሳል።
“በማደያዎች በየቀኑ ያለው የቤንዚን አቅርቦት በቂ ያልሆነ ወይም ሙሉ ለሙሉ የማይገኝ በመሆኑ አሽከርካሪዎች ረጅም ወረፋ ለመጠበቅ እንደሚገደዱ” ቤንዚን ለማግኘት እስከ ሶስት ቀን አልፎ ተርፎም አንድ ሳምንት ሊወስድ እንደሚችል አሽከርካሬዎች መናገራቸውም በዘገባው ተካቷል።
በተመሳሳይ በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ከተማ እና በአማራ ክልል አሽከርካሪዎች ለከፍተኛ የቤንዚን እጥረት መዳረጋቸውን የተመለከቱ ዘገባዎች ማቅረባችን ይታወሳል።
በአማራ ክልል የተፈጠረውን የቤንዚን እጥረት ተከትሎ አሽከርካሪዎች በኮታ እንዲቀዱ የሚያዝ መመሪያ መዘጋጀቱን የተመለከተ ዘገባ ለንባብ ካበቃናቸው ውስጥ ይገኝበታል። አስ