
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2017 ዓ/ም፦ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በአዲስ አበባ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፤ “ትግራይ ውስጥ ከሚፈጠር ትርምስ እናተርፋለን የሚሉ ብዙ ወገኖች አሉ፤ የኤርትራ መንግሥት አንደኛው እንደሆነ አውቃለሁ” ሲሉ ተናገሩ።
“የኤርትራ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር የመጀመሪያ ግጭት ውስጥ የገባው ፕሪቶርያን ከተስማማን በኋላ ነው” ሲሉ የተለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ “ከኤርትራ መንግሥት ጋር ሰላም እንፍጠር ማለት ኤርትራ በትግራይ ላይ የፈጸመችውን ጭፍጨፋ እንካድ ማለት አይደለም” ብለዋል።
አክለውም “ሁሉም የፖለቲካ ሀይል ወይም ጄኔራል ከኤርትራ ጋር ተግባብቼ የሆነ ነገር አደርጋለሁ የሚልም አርገን አንውሰደው። ጭር ካለ አደጋ ላይ እንወድቃለን ብለው የሚያስቡ ወገኖች ግን ራሳቸውን አገልጋይ አድርገው አቅርበዋል። ነገር ግን በተወሰነ መንገድ ይሄን ሐይል ለመጠቀም እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ቡድኖች እንዳሉ አውቃለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
የኤርትራ መንግሥት ፍላጎት “የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራን ይወራል ብለው በሚያስቡበት ሰዓት ትግራይን ማቀዝቀዣ “በፈር ዞን” እንዲሆን ማድረግ ነው፤ ጠንካራ አጋጣሚ ተፈጥሯል ብለው ካመኑ ከእኛ ሰዎች ጋር ሆኖ እንደገና ወደ አዲስ አበባ መጓዝ የሚቻልበትን መንገድ ማማተር ነው” ብለዋል።
በተጨማሪም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ክልሉ ላይ “የህግ ተቀባይነት ያጡ እና ከጦርነት ትርፍ እናገኛለን የሚሉና በጥቅም የተሳሰሩ የተወሰኑ የህወሃት ቡድን” የተወሰኑ ከፍተኛ መኮንኖችን በመያዝ ክልሉን አደጋ ላይ እየከተቱ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ እንቅስቃሴ “ትግራይን ወደ ሌላ የትርምስ ምዕራፍ እየወሰደ ይገኛል” ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ይህንን አስመልክቶ የፌዴራል መንግስት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስራውን እንዲሰራ “ደጋፍ እንዲያደርግ እንጂ ጦር አዝምቶ ጣልቃ እንዲገባ ጥያቄ አላቀረብንም” ብለዋል። በዚህ ደረጃ ጥያቄ ለማቅረብ የሚያስችል ሁኔታም የለም ብለዋል።
አቶ ጌታቸው፤ “ክልሉ ወደ ሌላ ጦርነት መግባት የለበትም። ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፌዴራል መንግስቱ ውሳኔ አካል ነው። የፌዴራል መንግስቱ አግባብነት ያለው ሃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል” ሲሉ ተደምጠዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ትላንት ባወጣው መግለጫ የፌዴራል መንግስት “አስፈላጊውን ድጋፍ” እንዲያደርግለት ጠይቋል። ከጥር 15 ቀን 2017 ጀምሮ አንዳንድ የትግራይ ሰራዊት ከፍተኛ አዛዦች የጥቂቶችን የስልጣን ጥማት ለማርካት ግልጽ የሆነ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ነበር” ሲል ያወሳው መግለጫው በዚህ ሳምንት ግን “በተለይ የሰሜን ምስራቅ እና ደቡብ ግንባር አዛዦች የሚመሩ ህገወጥ ድርጊቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል” ሲልም አስታውቋል።
ይህንን ተከትሎ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ትናንት 03 መጋቢት 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፤ “በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሶስተኛ ወገን ትግራይ ውስጥ እጁን እንዲያስገባ የሚያደርገው ጥሪ በፍፁም ተቀባይነት የለዉም” ሲል ተቃውሟል። በጊዜያዊ አስተዳደሩ አራት የሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች መታገዳቸው “ከሃላፊነት ውጪ የተደረገና ተፈፃሚነት የሌለው” ውሳኔ ነው ሲል ገልጿል።
የግዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት በሰጡት መግለጫ፤ የትግራይ ክልል ጦርነትን ዳግም በፍጹም ማስተናገድ እንደማይችል ጠቅሰው “ጥቅመኛ ቡድን ክልሉ ውስጥ ያለውን ሁኔታ የህዝብ ትርምስ ለማስመስል የሚያደርገው ጥረት ቢኖርም ወንበር ለማዳን ብሎ መስዋእትነት የሚከፍል ወጣት የለም” ብለዋል። ክልሉ “ጦርነትን አያስተናግድም፣ ህዝቡም ሆነ ታጣቂው ፍላጐት የለውም” ነው ያሉት።
በተገኘው የሰላም ምእራፍ ላይ ህዝቡ “እንዲንበረከክ ከመስራት ይልቅ እኔ ልንበርክከ” ማለት ይገባ ነበር ሲሉ ገልጸዋል።
አክለውም የትግራይ ህዝብ “ዳግም ወደ ግጭት እንዳይገባ” እና ሰላምን መፍጠር የሚቻልባቸው እድሎችን ማጽናት ይገባል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ህዝቡን ዳግሞ ግጭት ውስጥ መክተት ተጨማሪ ተፈናቃዮችን ማብዛት እንደሆነ ጠቅሰው፣ ይህን ለማስቀረት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ መተግበር እንደሚገባም ገልጸዋል።
“ስብሰባዎች ላይ የሚነሱት ማን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ርቋል የሚል ነው። የጊዜያዊ አስተዳደሩ በፌዴራል መንግስት በጀት የሚተዳደር በመሆኑ በቅርበት ነው የምንሰራው” በማለት፣ እንዲህ አይነት የፖለቲካ አባዜ ግን ተገቢነት እንደሌለው ተናግረዋል።
አቶ ጌታቸው የፌዴራል መንግስት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ጊዜያዊ አስተዳደሩን ያቋቋመ በመሆኑ፤ አስተዳደሩን የሚመራው ክልል አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የመከላከል ስልጣን አለው ብለዋል።
በፌዴራል መንግስቱ የተሾመን የክልል ፕሬዚዳንት “የቀድሞ” በሚል ስያሜ ከመጥራት ጀምሮ እያካሄዱት ያለው ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ክልሉን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ሊታረም የሚገባው ነው ብለዋል።
በትግራይ ክልል “እየተፈጠረ ያለው ቀውስ “በምርጫ ቦርድ ህጋዊ ተቀባይነት ያጣ የሕወኃት አንድ ህገ-ወጥ ቡድን” የስልጣን ፍላጎቱን በኃይል ለማሳካት የፈጠረው ነው” ሲሉም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።
በዚህም ክልሉ ወደ ቀውስ መግባቱን ገልጸው፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩም ችግሮችን ስርዓት ለማስያዝ በውስጡ ያሉ አቅሞችን እንዳይጠቀም እያደረገው መምጣቱን አስረድተዋል።
አሁን እየተደረጉ ያሉ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች ወደ ጦርነት እንዳያመሩና የጠላት መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ሁሉንም አይነት የመፍትሔ አማራጮች መተግበር እንደሚገባ አንስተዋል።አስ