ዜናፖለቲካ

ዜና: “በሰሓርቲ ወረዳ ነዋሪዎች በሰራዊቱ የተፈጸመ በደል የለም፣ የጸጥታ ሀይሉን እና አመራሩን ሆን ተብሎ ከህዝብ ለመነጠል እየተሰራ ነው” ሲል የክልሉ የጸጥታ ቢሮ አስተባበለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17/2017 ዓ.ም፡- በትግራይ ክልል የሚገኙ የጸጥታ ሀይሎችን እና አመራሮቻቸውን ስም በማጥፋት ሆን ተብሎ ከህዝብ ለመነጠል እየተሰራ ነው ሲል የትግራይ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም በሰሃርቲ ወረዳ የተፈጸመውን ሁከት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስተባበለ።

ባሳለፍነው ሳምንት የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ “የተወሰኑ የትግራይ ሠራዊት አመራሮች” ሲል የጠራቸው አካላት “የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር መዋቅር ለማፍረስ አግባብነት የሌለው ስራ እየሰሩ ይገኛል” ሲል መውቀሱን መዘገባችን ይታወሳል።

በክልሉ በምትገኘው ሰሓርቲ ወረዳ የቀበሌ አወቃቀሮች ላይ የሚገኙ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ተወካዮችን በአከባቢው የሚገኙ “የሰራዊቱ አባላት” የሀይል እርምጃ በመውሰድ መዋቅሮቹን የማፍረስ ስራ ተሰርቷል ሲል በአብነት የጠቀሰው መግለጫው ድርጊቱ የሚያሳዝን ነው ማለቱም በዘገባው ተካቷል።

የክልሉ የሰላምና የጸጥታ ቢሮ የካቲት 15 ቀን ባወጣው መግለጫ በሰሃርቲ ወረዳ ተፈጥሮ የነበረውን ሁከት እና ግርግር “ወደ ሌላ መልክ እና ደም አፋሳሽ ተግባር እንዳይቀየር” በማድረግ የጸጥታ ሀይሉ ሁኔታውን ለማርገብ ቻለ እንጂ በህዝቡ ላይ የፈጸመው አንዳችም በደል የለም ሲል አስተባብሏል፤ እንዲያውም በጸጥታ ሀይሎቹ ላይ ከባድ አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል ስም ማጥፋት ተፈጽሞብኛል ሲል ኮንኗል።

ውጥረቱ ሌላ መልክ እንዳይዝና ወደ ደም መፋሰስ እንዳይሸጋገር በመስጋት የአከባቢው ነዋሪዎች ባደረጉለት ጥሪ ወደ ቀበሌዋ በመግባት የማረጋጋት ስራ መስራቱን አስታውቋል።

“በየካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም በክልሉ በሚገኘው ደቡብ ምስራቅ ዞን ሰሃርቲ ወረዳ አዲስ አለም ተብላ በምትጠራ ቀበሌ የየራሳቸውን ማህተም አሰርተው የቀበሌዋ አስተዳዳሪ እኔ ነኝ በሚል ነዋሪውን ለሁለት እንዲከፈል አድርገው እና የየራሳቸውን ደጋፊዎች አሰልፈው ወደ አልሆነ ሁከት ሊያመሩ ሲሉ ከነዋሪዎች በቀረበ ጥሪ በአከባቢው የሚገኘው አርሚ 26 ጣልቃ በመግባት ሁኔታውን ለማርገብ መቻሉን” አስታውቋል።

“ጸጥታ አባላቱ ወደ አከባቢው በመግባት በሁለት አመራሮችና በደጋፊዎቻቸው የቀበሌዋ ነዋሪዎች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት መሃል በማግባት ሰራዊቱ የተፈጠረውን ሁከት፣ ግርግር እና ችግር ችለው ሁኔታውን አረጋጉት እንጂ በህዝቡ ላይ የፈጸመው አንዳች በደል የለም” ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

እንዲያውም “የጸጥታ አባላቱ ሁኔታውን አረጋግተው ወደ ቦታቸው በሚመለሱበት ወቅት ተፈጥሮ የነበረውን ግርግር ተጠቅመው የግል ፍላጎታቸውን ማስፈጸም ያቃታቸው ግለሰቦች ባደረሱባቸው ጥቃት በጸጥታ ሀይሉ ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን” ጠቁሟል።

የጸጥታ አባላቱ ለፈጸሙት ተግባር “ምስጋና የሚቸራቸው እንጂ ወቀሳ ሊቀርብባቸው፣ ኩነና ሊሰነዘርባቸው አይገባም” ብሏል።

በተጠቀሰው ቀበሌ እና ዕለት “ወንጀል ተፈጽሟል የሚል ጥርጣሬ ያለው ማንኛውም ወገን ካለ ከወገንተኝነት ነጻ የሆኑ አካላት በኮሚቴ ደረጃ አዋቅረው እንዲመረምሩ፣ ነጻ ሚዲያዎችም ወደ ቀበሌዋ እንዲሰማሩ እና አጣርተው ሃቁን ለህዝብ እንዲያቀርቡ” ጥሪ አቅርቧል።

በአከባቢው ስለተፈጠረው ችግር “ሁሉንም ነዋሪውን አሳትፎ እና ከሚመለከታቸው አካላት መሉ መረጃ በመውሰድ ማጣራት ሳይደረግ በአንዳንድ የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የጊዜያዊ አስተዳደሩ መዋቅሮች ሳይቀር ሁኔታውን አጋኖ በማቅረብ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተካሂዶብኛል” ሲል ተችቷል።

“በጸጥታ ሀይሉ ዙሪያ ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት እና ስሙን በማጥፋት ከህዝብ ለመነጠል የሚደረግ ከንቱ ድካም” ሲል ገልጿል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button