ዜናፖለቲካ

ዜና: የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደሩን መዋቅር ለማፍረስ የተወሰኑ የክልሉ የጸጥታ ኃይል አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14/2017 ዓ.ም፡- በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር “የተወሰኑ የትግራይ ሠራዊት አመራሮች” ሲል የጠራቸው አካላት “የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር መዋቅር ለማፍረስ አግባብነት የሌለው ስራ እየሰሩ ይገኛል” ሲል ትላንት የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ወቀሰ።

በክልሉ በምትገኘው ሰሓርቲ ወረዳ የቀበሌ አወቃቀሮች ላይ የሚገኙ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ተወካዮችን በአከባቢው የሚገኙ “የሰራዊቱ አባላት” የሀይል እርምጃ በመውሰድ መዋቅሮቹን የማፍረስ ስራ ተሰርቷል ሲል በአብነት የጠቀሰው መግለጫው ድርጊቱ የሚያሳዝን ነው ብሏል።

“የትግራይ ሰራዊት” የህዝቦቹን ህልውና ለማስጠበቅ የተሰለፈ እንጂ “የስልጣን ጥመኛ ቡድንን ፍላጎት ለማስፈጸም የሚንቀሳቀስ ሀይል አይደለም” ያለው መግለጫው “ከስነስርአት በአፈነገጠ ሁኔታ ሰራዊቱ የጊዜያዊ አስተዳደሩን መዋቅር ለማፍረስ በሚደረግ እንቅስቃሴ ሊሳተፍ አይገባም” ሲል አሳስቧል።

“ሁኔታው ​​በዚህ መልክ የሚቀጥል ከሆነ እንደ ህዝብ ልንወጣው ወደማንችለው ከባድ ቀውስ ውስጥ እንደምንገባ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለው ህዝባችን ሊገነዘበው ይገባል” ብሏል።

“የህግም ሆነ የአሰራር ክፍተቶች ቢኖሩም እንኳ” የአከባቢው ፖሊስ እና ሚሊሻ አባላት ከህዝባቸው ጋር በመሆን የሚፈቱት እና የሚያርሙት እንጂ “የሰራዊት አባላትን በየጣቢያው እየተሰማሩ የመንግስት መዋቅሮችን በማፍረስ ላይ መሳተፍ የለባቸውም፣ አይገባም” ሲል አሳስቧል።

“የትግራይ ሰራዊት” እነዚህን አንዳንድ የሰራዊት አመራሮች የሚፈጽሙትን የህግ ጥሰት ተረድቶ አደብ ግዙ እንዲላቸው የጊዚያዊ አስተዳደሩ ጥሪ አቅርቧል።

በተያያዘ ዜና በወረዳዋ የተፈጸመው ሁኔታ አስመልክቶ ቪኦኤ ባሰራጨው ዘገባ በጸጥታ ኃይሎች እና ነዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት 17 ሰዎች መጎዳታቸውን አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ጉዳቱ የደረሰው በወረዳዋ የአንድ ቀበሌ አስተዳዳሪ ማኅተም በኃይል ነጥቀዋል የተባሉ የፀጥታ አባላት ወሰዱት በተባለ ርምጃ መሆኑን የወረዳው አስተዳዳሪ እንደነገሩት አስታውቋል።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በወረዳ አስተዳዳሪነት የተሾሙት፣ አቶ አታኽልቲ ግርማይ “የፀጥታ አባላት ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወግነው ወደ ሕዝብ መተኮስ ሳይኾን፣ የሥራ ድርሻቸው ሰላም እና ፀጥታ መጠበቅ ነው” ማለታቸውንም አስደምጧል።

በድርጊት ፈጻሚነት የተወቀሰውና፣ “አርሚ 26” ተብሎ የሚጠራው የክልሉ የፀጥታ መዋቅር አዛዥ ኮሌኔል ሓጎስ ገብረ፣ የፀጥታ አባላቱ ወደ አከባቢው የገቡት በሕዝብ ጥሪ መኾኑን ገልፀው “በነዋሪዎች ላይ የተወሰደ እርምጃ የለም” ማለታቸውንም አካቷል። “ክሱ የሰራዊታችን ስም ማጥፋት ነው” ሲሉም ምላሽ መስጠታቸውን አካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button