
አዲስ አበባ፣ የካቲት 13/ 2017 ዓ.ም፡- በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በበቆጂ ከተማ እና በሽርካ ወረዳዎች መካከል በሚገኘው በጋላማ ተራራ ላይ ከሳምንት በፊት የተከሰተው የደን ቃጠሎ አሁንም መቆጣጠር እንዳልተቻለ እና ከመንግስት በኩል ምንም አይነት ምላሽ አለመሰጠቱን ነዋሪዎች ገለጹ።
በደኑ አቅራቢያ ነዋሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ የቃጠሎው መንስኤ እስካሁን አለመታወቁን ገልጸው ከአንድ ሳምንት በላይ እየነደደ መሆኑን አረጋግጠዋል።
“ደኑ ለአንድ ሳምንት ያህል ሲቃጠል የቆየ ሲሆን አሁንም እየነደደ ነው” ያሉት ነዋሪው አክለውም የአካባቢው ማኅበረሰብ እሳቱን ለማጥፋት ያደረገው ጥረት አከባቢው ባለው አስቸጋሪ የመሬት አቀማመጥ የተነሳ መደናቀፉን ተናግረዋል።
አያይዘውም እስካሁን ድረስ ከመንግስት አካላት በኩል ምንም ዓይነት ምላሽ አለመሰጠቱን ጠቅሰው እሳቱ በዚሁ ሁኔታ ከቀጠለ በርካታ የተፈጥሮ መስህቦችን ሊያጠፋ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ሌላኛው የዓይን እማኝ በበኩላቸው ደግሞ እሳቱ በስፋት እንደተሰራጨና ጭሱም ከሩቅ እንደሚታይ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
አክለውም በኦሮሚያ ክልል የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ የተለያዩ የዱር እንስሳት ዝርያዎች የሚገኙበት ደን መሆኑን በመግለጽ ጉዳዩ በአስቸኳይ ምላሽ የሚፈልግ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
“ይህ የህዝብ ሀብት በመሆኑ መንግስት የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት” ያሉት ነዋሪው ይሁን እንጂ እሳቱ ከሳምንት በላይ ቢሆነውም ከመንግሥት በኩል አስፈላጊው ምላሽ ባለመስጠቱ ማዘናቸውን ገልጠዋል።
የአርሲ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት ሂርጳ ዳባ በበኩላቸው ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን እሳቱ ለአንድ ሳምንት ያህል መቆየቱን ገልጸው ሆኖም “ቀጣይነት ያለው አይደለም” ብለዋል።
የአካባቢውን ማህበረሰብ በማሳተፍ እሳቱን ለማጥፋት ርብርብ መደረጉን አንስተው ሆኖም በጫካው ሰፊ ሽፋን እና አስቸጋሪ የመሬት አቀማመጥ የተነሳ ሙከራዎቹ በተጠበቁት መጠን ስኬታማ እንዳልሆኑ ገልፀዋል።
እሳቱ ቀይ ቀበሮ፣ ኒያላ፣ ከርከሮ፣ ዝንጀሮዎችን ጨምሮ በርካታ የዱር እንስሳትን አደጋ ላይ እንደሚጥል እና መስፋፋቱን ከቀጠለ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ ከኦሮሚያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ቃጠሎውን ለመቆጣጠር በሚወሰዱ እርምጃዎች ዙርያ በአሰላ ከተማ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል። አስ