
አዲስ አበባ፣ የካቲት 14/2017 ዓ.ም፡- በትግራይ ሰራተኞች ያልተከፈላቸውን ውዝፍ ክፍያ ጋር በተያያዘ ክስ እንዳይመሰርቱ በጊዜያዊ አስተዳደሩ የጸደቀውን ደንብ የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውድቅ እንዳደረገው ተገለጸ።
የትግራይ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ የወጣውን እና ውዝፍ ክፍያ ጋር ምንም አይነት ክስ እንዳይመሰረት የሚያግደውን ደንብ 4/2016 ውድቅ በማድረግ ክሱ እንዲቀጥል ትዕዛዝ መስጠቱን ከትግራይ ቴሌቪዢን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ብይኑን የሰጠው በትግራይ መምህራን ማህበር የ17 ወራት ውዝፍ ክፍያን አስመልክቶ ከሳሹ (የመምህራን ማህበሩ) ባቀረበው የመጀመርያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ መሆኑን ዘገባው አስታውቋል።
ስለዚህም በትግራይ መምህራን ማህበር የቀረበው ከውዝፍ ክፍያ ጋር የተያያዘው ክስ ይቀጥላል ተብሏል።
በክሱ ላይ አንደኛ ተከሳሽ የክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ ሁለተኛ ተከሳሽ የትግራይ ፋይናንስ ቢሮ፣ ሶስተኛ ተከሳሽ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና አራተኛው ተከሳሽ ደግሞ የገንዘብ ሚኒስቴር ናቸው፤ 4ኛ ተከሳሽ በችሎቱ ባይቀርብም ጉዳዩ ተከሳሹ በሌሉበት እንዲታይ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን በከሳሽ እና በተከሳሹ መካከል ያለው ክርክር መቀጠሉ ተጠቁሟል።
ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ ህዳር ወር 2015 ዓ.ም ድረስ ያልተከፈለ ውዝፍ ክፍያ ጋር በተያያዘ የቀረበው ክስ እንዲታገድ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ መወሰኑን ዘገባው አስታውሷል።
ክሱ እንዲቋረጥ ማድረግ እና የክፍያ ጥያቄ ክስ ሁለት የሚቃረኑ ሀሳቦች ናቸው ያለው ፍርድ ቤቱ የዜጎች መሠረታዊ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ከአለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት መተርጎም እንዳለባቸው በሕገ መንግሥቱ ስለሚደነግግ፤ ማንኛውም ሰው በሕገ መንግሥቱም ሆነ በሌሎች ሕጎች የተሰጡት መብቶች ከተነፈገ ስልጣን ባላቸው ሀገራዊ አካላት ፍትሕ የማግኘት መብት አላቸው ሲል ገልጿል።
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በትግራይ መምህራን ማህበር የቀረበው ክስ እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የትግራይ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከራካሪዎቹ መካከል የቀረቡ ሀሳቦችን መሰረት በማድረግ ከሳሽ ጥር 14 ቀን አሻሽሎ ባቀረበው ክስ መሰረት ምስክሮቹን አቅርቦ እንዲያሰማ የህግ ትዕዛዝ ይጻፍ በማለት ለመጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱን ዘገባው አመላክቷል።
የትግራይ ክልል መምህራን ማህበር የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና የፌደራል መንግስቱ ለክልሉ መምህራን የ17 ወራት መከፈል የነበረባቸውን ደመወዝ አልከፈሉም የሚል በነሀሴ ወር 2016 ዓ.ም ሁለቱ አካላት ላይ ክስ መመስረቱን መዘገባችን ይታወሳል።
በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና በፌደራል መንግስት ላይ የቀረበው ክስ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እየታየ እንደሚገኝ የክልሉ መምህራን ማህበር ጠበቃ የሆኑት አቶ ዳዊት ገብረሚካኤል ለአዲስ ስታንዳርድ መናገራቸውን ዘገባው አካቷል።
“ክስ ከተመሰረተባቸው መካከል የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የክልሉ ትምህርት እና ፋይናንስ ቢሮዎች ይገኙበታል፣ ክሱም የፌደራል መንግስት ለመምህራን የላከውን የአምስት ወር ደሞዝ ለሌላ አገልግሎት በማዛወራቸው የተሰጣቸውን ስልጣን ያለአግባብ ተጠቅመዋል” የሚል ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በተጨማሪ የፌዴራል መንግስት ደግሞ “የ12 ወራት ደሞዝ ባለመልቀቁ ነው ክሱ የተመሰረተው” ሲሉ አቶ ዳዊት አስረድተዋል፡፡
“መምህራኑ ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውና መፍትሄ የሚሰጣቸው አካል ባለመኖሩ ለስቃይና እንግሊት ተዳርገዋል፤” ሲሉ አብራርተዋል አቶ ዳዊት።
በሌላ በኩል በክልሉ በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ውድመት እንደደረሰበት የተገለጸው የትግራይ ክልል፣ የትምህርት ዘርፍን ሙሉ ለሙሉ መልሶ እንዲያገግም ለማስቻል 5 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ መገለጹን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።
ይህ የተገለጸው የክልሉ የትምህርት ዘርፍ ስለሚገኝበት ሁኔታ፣ በጦርነቱ ስለደረሰበት ውድመት፣ እንዲሁም ሙሉ ለሙሉ ለማገገም የሚያስፈልጉ ሥራዎችን በተመለከተ የትምህርት ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር በተወያየበት ወቅት መሆኑን ተጠቁሟል። አስ