
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12/2017 ዓ.ም፡- የአማራ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ የዳኞች ያለመከሰስ መብት ማጽደቁ ዳኞች ከማናቸውም ውስጣዊ እና ውጫዊ ተጽዕኖዎች ተላቀው ስራቸውን እንዲከውኑ ለማስቻል አንድ እርምጃ ነው ሲል በአዎንታነት እንደተቀበለው የክልሉ የዳኞች ማኅበር ሰብሳቢ ብርሐኑ አሰሳ ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።
ከዚህ በፊት ጥያቄው በተደጋጋሚ ሲነሳ መቆየቱን የገለጹት አቶ ብርሐኑ፣ ሁለት ጊዜ ያህል ምክር ቤት ቀርቦ ውድቅ መደረጉን አስታውሰዋል።
በክልሉ የሚገኙ ዳኞች በተደጋጋሚ ለእስር እና ወከባ ተጋላጭ እንደነበሩ ገልጸው ማህበሩ ለሚመለከታቸው ሁሉ በደብዳቤ ሲያስታውቅ መቆየቱን አንስተዋል።
በተጨማሪም ከዚህ በፊት በክልሉ ታስረው ከነበሩ 13 ዳኞች መካከል ስምንቱ መለቀቃቸውን አስታውቀው ቀሪ አምስት ዳኞች አሁንም በእስር ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሰጡት የፍርድ አፈጻጸም ውሳኔ ላይ ያላግባብ ትዕዛዝ ሰጥታችሗል ተብለው ዳኞች ከችሎታቸው ተነስተው ተወስደው ትዕዛዙን እንዲያነሱ የተገደዱባቸው ሁነቶች ብዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
“በተለያዩ ወረዳዎች ላይ በሰጧቸው ትዕዛዞች ምክንያት እና በፍርድ አፈጻጸም ሂደት አንዳንድ ጊዜ አመራሮቹ ዳኞቹን እንዲፈፅሙ ሲያዟቸው አንፈጽምም ሚሉባቸው አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ አመራሮቹ ለምን እስር ትዕዛዝ ወጣብን በሚል በጸጥታ ሃይሎች አማካኝነት ዳኞች እንዲታሰሩ የሚያደርጉበት ሁኔታ አለ። ይሄ በጣም ብዙ ነው አንድ ሁለት የሚባል አይደለም። ስለዚህ ህጉ መጽደቁ እነዚህን ጉዳዮች ከሞላ ጎደል ያስቀራል ብለን ተስፋ የምናደርገው ነው።” ሲሉ የህጉን መጽደቅ አዎንታዊነት አስረድተዋል።
ዳኞች በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ባሉበት ባሁኑ ሰዓት ህጉ መጽደቁ ለዳኞች ደስታን የፈጠረና ስራቸውን ተረጋግተው ለመስራት የሚያስችላቸው አንድ ግብአት ነው ሲሉ ሰብሳቢው ተናግረዋል።
“ያለመከሰስ መብት የዳኝነት ነፃነትን በተመለከተ ህገመንግሥቱ ያስቀመጠው መብት ነው። ዳኞች ነፃና ገለልተኛ ሆነው ጉዳዮቻቸውን እንዲወስኑ ለማስቻል የህግ ጥበቃ ይሰጣቸዋል ማለትም ዳኞች የሚወስኗቸው ውሳኔዎች ከፍርሃት ጣልቃ ገብነት እንዲሁም ከማንኛውም ውስጣዊ ሆነ ውጫዊ ተጽዕኖዎች ነጻ ሆነው ስራዎቻቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ለማስቻል የዳኝነት ነጻነት ተብሎ በህግ ጥበቃ የተሰጠው መብት ማረጋጋጫ አካል ነው” ብለዋል።
የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር የዳኞች እስርን በተመለከተ ዳኞች በሚሰጧቸው ውሳኔዎች የተነሳ ለእስርና እንግልት መዳረግ የለባቸውም በማለት በተደጋጋሚ ሲጠይቅ መቆየቱን አስታውቀዋል።
“በዚህ ዓመት የዳኞች ማህበር የዳኞችን እስር በተመለከተ ዳኞች ሊታሰሩ አይገባም ብለን የምናወጣቸው መግለጫዎች አብዘሃኞቹ የሚገናኙት ዳኞች በሰጧቸው ውሳኔዎች ምክንያት እንዲሁም በሰጧቸው ትዕዛዞች የተነሳ በመታሰራቸው ነው። ስለዚህ በጣም በርካታ ጉዳዮች አሉ ዳኞቹ በከፍተኛ ሁኔታ እየታሰሩ ነው የሚል እሮሮ ስናቀርብ ነው የከረምነው። የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም በተለያዩ ጊዜያት ባወጣው ሪፖርቶች ሲገልጽ ቆይቷል።” ብለዋል።
በመሆኑም የህጉ መጽደቅ ዳኞቹ ነጻ እና ገለልተኛ ሆነው ስራቸውን እንዲሰሩ እንደሚያስችላቸው ገልጸው ይህም እንደአጠቃላይ የፍትሕ ስርዓቱ ላይ፣ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ፣ የህግ የበላይነት ማረጋገጥ ሂደት ላይና እንዲሁም በሰብአዊ መብት መከበር ላይ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አበክረዋል።
አክለውም “ህጉ በደንብ ክትትል ተደርጎበት ተፈጻሚ መሆን ከቻለ በአጠቃላይ የፍትሕ ስርዓቱ ላይ ይዞ የሚመጣው ለውጥ ቀላል አይደለም” ብለዋል።
ይሄ ደግሞ የሁሉም የአስፈጻሚውም፣ የህግ ተርጓሚውም፣ የህግ አውጪውም ሃላፊነትም ጭምር መሆኑን አመልክተዋል።
ሌላኛዋ የጠቅላይ ፋርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ሳባ አበረ በበኩላቸው ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ የዳኞች ያለመከሰስ መብት ጉዳይ ለረጅም ጊዜ ሲጠየቅ የነበረ ጉዳይ መሆኑን አንስተው በስተመጨረሻ ህጉ ሊጸድቅ ችሏል ብለዋል።
ህጉ እስከዛሬ ተቀባይነት ሳይኖረው የቀረው “ዳኛው በቃ እንደ ልቡ ይሆናል፣ ስራውን በአግባቡ አይሰራም፣ ለወንጀል መስራት ምቹ ሁኔታ ይፈጥርለታል” በሚል የተሳሳተ ግምት እንደነበር ጠቁመዋል።
“የፍርድ ቤት ስራ አንዱን አስደስቶ ሌላውን የሚያስከፋ በመሆኑ ሁሉንም ተከራካሪ ወገን የሚያስደስት አይደለም። በተለይ መሳሪያ ይዘው የማሰር ስልጣን የተሰጣቸው አካላት ከፍርድ ቤቶች ጋር በሚኖራቸው መስተጋብር ብዙ ጊዜ ግጭቶች ይፈጠራሉ።” ያሉት ዳኛዋ ከዚህ በፊት ዳኞች ምንም ወንጀል ሰርተዋል ተብለው ባልተጠረጠሩበት ሁኔታ ከችሎት ሳይቀር እየጎተቱ ማሰር በተለይ በአማራ ክልል የተለመደ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የህጉ መጽደቅ መሰል ነገሮችን ያስቀራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።
አያይዘውም ያለመከሰስ መብት (Immunity) ማለት ዳኞች በፍጹም አይከሰሱም ማለት ሳይሆን በስራቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን ጫና የሚቀንስ እና የዳኝነት ነጻነቱ እንዳይሸረሸር በህግና ህግ ብቻ ተመስርተው እንዲሰሩ ከለላ የሚሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ተፈጻሚነቱን በተመለከተ ሲናገሩም በመጀመሪያ ህጉ መውጣቱ ትልቅ ነገር ነው፣ ሁሉንም ነገር የሚገዛው ህግ ነው። የትኛውም አካል በህግና ሥርዓት ነው የሚገዛውና ዋናው ነገር የህግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
ለተፈጻሚነቱም እስከታች ያለው የጸጥታ መዋቅር ህጉ እውቅና እንዲኖረው ማድረግ እና ፍርድ ቤቶችም የራሳቸውን ሚና መጫዎት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችም በሰፊው በጠቅላይ ፍርድ ቤት አማካኝነት እንደሚካሄድ ገልጸው “እንደማንኛውም ህጎች እክል አይገጥመውም ማለት አይደለም ግን ገና የጸደቀ በመሆኑ ውጤቱን በጋራ የምንመለከተው ይሆናል” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም አዲስ ስታንዳርድ በአማራ ክልል የሚገኙ ዳኞች እየደረሰባቸው የሚገኙ ተግዳሮቶችን መዘገቡ ይታወሳል።
ለአብነትም በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም. በክልሉ የሚገኙ ከ35 በላይ ዳኞች አግባብነት በሌለው ሁኔታ ታስረው በኋላ የተለቀቁ መሆናቸውን የአማራ ክልል ዳኞች ማህበርን ዋቢ አድርገን ዘግበናል።
ባሳለፍው ዓመት በክልሉ የሚገኙ ዳኞች እስር መጨመሩን ዘገባው አመልክቷል።
በቅርቡ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ 89 ዳኞች ከስራቸው መልቀቃቸውን አስታውቋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ዓለም አንተ አግደው ሰሞኑን በተካሔደው የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት፣ የደኅንነት እና የጸጥታ ስጋት እንዲሁም የክፍያ ማነስ በመንፈቅ ዓመቱ በርካታ ዳኞች ከሥራ መልቀቅ ምክንያት መሆኑንም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም 28 የወረዳ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎቶች አገልግሎት መቋረጡንም አመልክተዋል። አስ