ዜናፖለቲካ

ዜና፡ የሰለም ስምምነት ለተፈራረሙ ሶስት የቀድሞ ኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች ሹመት ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14/ 2017 ዓ/ም፦ የኦሮሚያ ክልል መንግስት በህዳር ወር ከመንግስት ጋር የሰለም ስምምነት ለተፈራረሙ ሶስት የቀድሞ ኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች ሹመት መስጠቱን አስታወቀ፡፡

በዚህ መሰረትም የቀድሞ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የማዕከላዊ ዞን አዛዥ የነበሩት ያደሳ ነጋሳ (በትግል ስሙ ጃል ሰኚ) በቢሮ ሃላፊ ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ተደርገው ተሾመዋል።

በተጨማሪም አቶ ኦሮሚያ ረቡማ የኦሮሚያ ክልል ዓቃቤ ሕግ ምክትል ሃላፊ ሆነው የተሾሙ ሲሆን አቶ ቶሌራ ረጋሳ የኦሮሚያ ክልል ጸጥታና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሆነው መሾማቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር ከነበሩት ጃል ሰኚ ነጋሳ መካከል ትላንት ህዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን ይታወሳል

የኦሮምያ ክልል መንግስት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የማዕከላዊ ዞን የቀድሞ አዛዥ ጃል ሰኚ ነጋሳ መንግሥት ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል የሰላም ስምምነት ፈርመዋል ሲል በወቅቱ ገልጿል።

ይህን ተከትሎ በጃል መሮ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት የፈረሙት ከወራት በፊት በስነምግባር ጉድለት ካባረርኳቸው አመራር ጋር ነው ሲል ማስታወቁ ይታወሳል

“ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አፈንገጠው የወጡ ተደርጎ በመንግስት በኩል እየቀረበ ያለው መረጃ ፍጹም ሀሰት ነው” ሲል የገለጸው መግለጫው የህዝቡን ስነልቦና ለመግዛት በሚል በመንግስት በኩል የቀረበ ማታለያ ነው ሲል ተችቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ቡድኑ በመግለጫው “ከወራት በፊት የተባረሩትን አባላት በማሰባሰብ እንድ ቪኦኤ እና ቢቢሲ የመሳሰሉ መገናኛ ብዙሃንን በመጋበዝ ከሰራዊቱ የከዱ በማስመሰል ዘገባ ቢያሰራም ትኩረት ሳያገኝ ቀርቷል” ሲል ገልጿል።

“አሁን ደግሞ ከነዚህ አካላት ጋር ሰላም ስምምነት ፈጽሚያለሁ እያለ የክልሉ መንግስት ህዝቡን እያሳሳተ ነው” ሲል ኮንኗል፤ “የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማሳሳት የተጠቀመበት ነው” ሲል ገልጿል።

ከዚህ ቀደም ብሎ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ/ም በጃል መሮ ወይም ኩምሳ ድሪባ ከሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ራሳችንን አግልለናል ሲሉ የድርጅቱ የቀድሞ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የማዕከላዊ ዞን የቀድሞ አዛዥ ጃል ሰኝ ነጋሳ ገልጸዋል

ጃል ሰኝ ነጋሳ፣ ከተመረጡ መገናኛ ብዙሀን ዘጋቢዎች በስልክ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በጃል መሮ ወይም ኩምሳ ድሪባ ከሚመራው ቡድን ተለይተው የወጡበትን ምክንያት ሲያስረዱ ” ህግና ደንብ የሌለበት እንዲሁም መተዳደሪያ ደንብ የሌለው ድርጅት ነው፣ ጥፋት ሲሰራም ተጠያቂነት የሌለበት ድርጀት ነው፤ በአንደ ሰው የሚመራ መሆኑን አይተንና ተረድተን ወደ ድርጀቱ ደንብና ህግ ተመልሰን እርስ በርሳችን እናሰተካክል ብለን ነው የምንቀሳቀሰው” ብለዋል።

በኦሮሚያ የቀጠለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ ነን ሲሉም ጃል ሰኝ መሰከረም 16 ቀን 2017 በሰጡት በዚሁ መግለጫ ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ በህዳር ወር ላይ ከክልሉ መንግስት ጋር ባደረጉት የሰላም ስምምነቱ ፊርማ ስነስርአት ላይ አቶ ሽመልስ የኦሮሞ ሕዝብ በባህሉ መሰረት ሰላም ይውረድ ብሎ ያቀረበውን ጥሪ ተቀብላችሁ በመምጣታችሁ በክልሉ መንግሥት ስም አመሠግናለሁ ብለዋል። የመከላከያ ሠራዊቱ ለሰላም ስምምነቱ ላበረከተው አስተዋፅኦም አቶ ሽመልስ አመሥግነዋል፡፡አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button