
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18/2017 ዓ.ም፡- ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ሀገራት የህዳሴ ግድብን እንደሚጎበኙ አስቀድማ ለአባል ሀገራቱ ማሳወቋን ተከትሎ ግብጽ በደብዳቤ አንዳትጎበኙ የሚል ደብዳቤ ልካ እንደነበረ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) አስታወቁ፤ አባል ሀገራቱ የግብጽን እንዳትጎበኙ ጥያቄ ወደ ጎን በማድረግ የኢትዮጵያን ጥያቄ መቀበላቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ በአዲስ አበባ በተካሄደው የናይል ተፋሰስ አባል ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የታደሙት አባል ሀገራቱ ወደ ናይል ቀን ስብሰባ ሲመጡ እግረ መንገዳቸውን የዓባይ ግድብንም እንዲጎበኙ አስቀድማ ደብዳቤ መላኳን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) አስታወቁ።
በአንጻሩ የግብፁ የውሃ ሚኒስትር ለሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ በኩል የተላለፈላቸውን የዓባይ ግድብን ጎበኙ ጥሪ መቀበል የለባችሁም ሲሉ በደብዳቤ መግለጻቸውን ጠቁመዋል።
‘መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የአገራቱ አምባሰደሮች እና ዲፕሎማቶች ግብፅ ያቀረበችውን የህዳሴውን ግድብ እንዳትጎበኙ ጥሪ፣ ማስጠንቀቂያ እና ዛቻ ወደ ጎን ትተው የህዳሴውን ግድብ ጎብኝተዋል።
እኛ በደብዳቤ ለታጀበው የግብፅ የ”አትጎብኙ” መልዕክት የመልስ ምት አልሰጠንበትም ያሉት ሚኒስትሩ፣ ጉዳዩ የተለመደ የሐሰት ፕሮፖጋንዳቸው አካል እንደመሆኑ ንቀን አልፈነዋል ብለዋል። ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን፣ የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮችም ምላሽ ሳይሰጡበት ያለፉት ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።
እንደ ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር) ገለጻ፤ የዓባይ ግድብ እንዳይጎበኝ በግብፁ የውሃ ሚኒስትር የቀረበው ጥያቄ ትርጉሙ ለሌሎች የተፋሰሱ ሀገሮች ያላቸውን ንቀት ማሳያ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ግድቧን ለማስጎብኘት መጋበዝ መብቷ እንደሆነ ሁሉ፤ እነርሱም የኢትዮጵያን ግብዣ መቀበል አለመቀበል መብታቸው ነው ብለዋል።
በዚህ ረገድ በመጀመሪያም ቢሆን የዓባይ ግድብን እንዲጎበኝ የጋበዘችው ኢትዮጵያ እንጂ የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፤ የግብፁ የውሃ ሚኒስትር የአትጎብኙ መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉም አንድም ሀገር እንዳልተቀበላቸው ተናግረዋል። “ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ነው። ግብፅም በኢትዮጵያ ሜዳ ለመጫወት ፈልጋ በራሷ ላይ ግብ አስቆጥራለች፤ ይሄም የአደባባይ ምስጢር ለመሆን ችሏል።” ብለዋል። ይሄ ደግሞ ለግብፅ አላስፈላጊ ጥይት ተኩሳ እራሷን እንደማቁሰል የሚቆጠር ነው ብለዋል።
“አስገራሚው ነገር እንዳትሔዱ ብለው ያሏቸው ሚኒስትሮች ወደ ዓባይ ግድብ የሔዱት እንዲያውም በከፍተኛ ተነሳሽነት ነው። ለስብሰባው የመጡት በሙሉ (የታንዛኒያው የውሃ ሚኒስትር በሀገራቸው ከምርጫ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ባጋጠማቸው አስቸኳይ ሥራ ከመሄዳቸው በስተቀር) ሁሉም የዓባይ ግድብን በሚኒስትር ደረጃ ጎብኝተዋል። በጉብኝቱም ሁሉም ለነበራቸው ጥያቄ ምላሽ አግኝተውበታል።
ሚኒስትሮቹ ዓባይ ግድብ ከደረሱ በኋላ የነበራቸው አግራሞት በግልጽ የሚታይ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ፤ ቀደም ሲል ሲነዛ የነበረው ፕሮፓጋንዳ እና መሬት ላይ ያዩት እውነታ ልዩነቱ አስደንቋቸዋል ብለዋል። ያንን የሚያክል ግድብ ኢትዮጵያ መገንባት መቻሏ እንደ ተዓምር የሚታይ ነው የሚል አስተያየትም መስጠታቸውንም ገልጸዋል።
የተፋሰሱ ሀገራት ሚኒስትሮች የግብፅን ጥሪ ባለመቀበል የዓባይ ግድብን ጎብኝተው ከሰማይ በታች፤ ከምድር በላይ አለኝ የሚሉትን ጥያቄዎቻቸውን ሁሉ ጠይቀው ምላሽ ማግኘት ችለዋል ሲሉ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ከፕሬስ ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።።
ጉብኝቱ፣ በተለይ ግብፅ ለሌላ ጊዜ የምትናገረውን ንግግር አስባበት እንድትናገር ያደረገ ጭምር ነው ብለዋል። ቀደም ሲል እንዲጎበኙ ታስበው የነበሩ ሃያ ሰዎች ቢሆኑም፤ ከግብፁ ሚኒስትር የአትጎብኙ ጥሪ በኋላ የሰው ቁጥር ወደ 30 ከፍ ማለቱም ለጉብኝቱ ከፍ ያለ ትኩረት የሰጡት መሆኑን የሚያመላክትም ነው ብለዋል። አስ