
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17/ 2017 ዓ/ም፦ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን (ኦፌኮ) “የኦሮሞ ነጸነት ሠራዊትን ያካተተ ክልላዊ የጋራ የሽግግር መንግስት” እንዲያቋቁሙ ኃላፊነት መረከባቸው ተገለፀ።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን (ኦፌኮ) ከተለያዩ የኦሮሞ ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ከየካቲት 12 እስከ 16 የ የአራት ቀን ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ያለውን የፖለቲካ እና የጸጥታ እና ሰብዓዊ ቀውስ መፍታት ላይ ባተኮረው ውይይት፤ የኦሮሞ ነጸነት ሠራዊት “የኦሮሚያን ድንበር በሽግግር መንግሥት አስተዳደር ስር” እንዲጠብቅ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ኦፌኮ እና ኦነግ ኃላፊነት መውሰዳቸውን ኦፌኮ ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ከውይይቱ በኋላ በወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ያለው ግጭት እንዲቆም እና የህዝቡም ሰላም አስተማማኝ በሆነ መንገድ እንዲጠበቅ ኦፌኮ እና ኦነግ የቻሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ አደራ እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ያለውን የፖለቲካ እና የአስተዳደር ችግር ለመፍታት “የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ እና ነጻ በሆነ መልኩ መንግስት እስኪመርጥ ድረስ የኦሮሚያ ፓርቲዎችን እና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት ያካተተ የኦሮሚያ የጋራ ሽግግር መንግስት ኦፌኮ እና ኦነግ እንዲያቋቁሙ ከስምምነት ላይ መደረሱም ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት ከመንግስት ጋር ግጭት ውስጥ የሚገኘው “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) በሽግግር መንግስቱ ኃላፊነት ወስዶ የኦሮሚያን ህግ፣ ሰላምና ድንበር መጠበቅ እንዲችል ሁለቱ ፓርቲዎች አስፈላጊውን ዝግጅት እንደሚያተባብሩ በመግለጫው ተመላክቷል።
የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ድንበር ችግር መፍታትን በተመለከተ “አዲስ አበባ በታሪክም ሆነ በህግ የኦሮሞ ህዝብ ንብረት እና የኦሮሚያ ዋና ከተማ መሆኗን ሙሉ በሙሉ በማመን ተጠሪነቷ ለኦሮሚያ መንግስት እንዲሆን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን (ኦፌኮ) ሃላፊነት ወስደው እንዲረጋግጡ ከመግባባት ላይ ተደርሷል።
በተጨማሪም ወሎ፣ ድሬ ዳዋ፣ መተከል፣ ሞያሌ፣ መደ ወላቡ ከተሞችን እና የመሳሰሉት አካባቢዎችን ጉዳይ በተመለከተ “በተለያዩ መንገዶች ተቆርጠው በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በሚገኙ ክልሎች ውስጥ የቀሩ የኦሮሚያ ድንበሮች በአለም አቀፍ ህግና በሀገሪቱ ህግ መሰረት ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲመለሱ” ለማድረግ ኃላፊነቱን ወስደዋል።
የገዳ/ሲንቄ ስርዓትም የኦሮሞ ፖለቲካ፣ ባህል እና የማህበረሰብ አንድነት መሰረት ሆኖ እነደሚቀጥል እና ፓርቲዎቹ ስርዓቱን ለማዘመን እንደሚሰሩም ተገልጿል።
በውይይቱ አንድም የመንግስት ባለስልጣናት ያልተሳተፉ ሲሆን የኦሮሚያ ክልልም ሆነ የፌዴራል መንግስት ውይይቱን ተከትሎ የወጣውን መግለጫ በተመለከተ የሰጡት አስተያየት የለም። በተጨማሪም በስምምነቱ ውስጥ ስሙ የተጠቀሰው የታጠቀው ቡድን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ውይይቱን እንደማይደግፍ ደጋግሞ ሲገልጽ ቆይቷል። አስ