
አዲስ አበባ፣ የካቲት 20/2017 ዓ.ም፡- ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከኤርትራ መንግስት ጋር ድብቅ ግንኙነት እንደጀመርኩ በማስመሰል የስም ማጥፋት ዘመቻ እየተካሄደብኝ ነው ሲል ትላንት የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.መ አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ አስስታወቀ።
በስም ማጥፋት ዘመቻው ላይም “የክልሉ የፀጥታ ሃይል” ሰለባ ነው ሲል የገለጸው ህወሓት የስም ማጥፋት ዘመቻው “ከሃቅ የራቀ እና ምንም አይነት ማስረጃ ሊቀርብበት የማይችል ነው፣ ተቀባይነት የለውም” ብሏል።
“ህወሓት እና የትግራይ ፀጥታ ሃይል ከኢትዮጵያ መንግስት ተቃራኒ ሁነው ለመሰለፍ ከኤርትራ መንግስት ጋር ይገናኛሉ የሚል ማባሪያ የሌለው የስም ማጥፋት ክሶች ተሰንዝረውብኛል” ብሏል።
የስም ማጥፋት ክሶች በመንዛት ላይ ናቸው ብሎ ከዘረዘራቸው አካላት ውስጥም በስም ያልጠቀሳቸው የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ሲል የገለጻቸው ይገኙበታል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም በአልጀዚራ ላይ ባስነበቡት ጽሁፍ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በአሁኑ ወቅት በህወሓት መሪዎች መካከል የተፈጠረውን ክፍፍል ሊጠቀሙበት እንደሚፈልጉ እና የተወሰኑ የህወሓት ባለስልጣናት ከኤርትራ ጋር ግንኙነት እየፈጠሩ ነው ሲሉ መግለጻቸውን መዘጉ ይታወሳል።
በጉዳዩ ዙሪያ የኤርትራ መንግሥት የማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረ መስቀል በኤክስ ገጻቸው የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ባስተላለፉት መልዕክት “የኢትዮጵያ ውስጣዊ ቀውሶች በአስመራ ላይ ሊላከኩ አይገባም” ሲሉ ገልጸው ኢትዮጵያ ቀጣናውን “የከበቡት” ችግሮች “መፍለቂያ እና ማዕከል ናት” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን መዘገባችን የታወሳል።
ከመንግስት ባለስለጣናት በተጨማሪ ባሳለፍነው አመት ነሃሴ ወር በሓውልቲ አዳራሽ በተካሄደው ጉባኤ ያልተሳተፈውን ቡድን የስም ማጥፋት እየነዛብኝ ነው ብሎ በክህደት ፈርጆታል።
‘አፍሪካ ኢንተለጀንስ’ እና ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (OMN) ደግሞ የስም ማጥፋት ዘመቻ እያካሄዱብኝ ነው ብሎ የጠቀሳቸው ሚዲያዎች ናቸው።
አፍሪካን ኢንተለጀንስ በቅርቡ ባስነበበው ዘገባው “ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የትግራይ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች ከኤርትራ ወታደራዊ ባለስልጣናት ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት እየጨመሩ መጥቷል” ሲል አስታውቋል።
እንደ ዘገባው ከሆነ የትግራይ እና የኤርትራ ከፍተኛ የጦር አመራሮች “በጥር ወር መጨረሻ አከባቢ በአስመራ ምስጢራዊ ስብሰባ አካሂደዋል” ።
የተጀመረውን የሰላም ሂደት (ስምምነት) በግልፅ የሚፃረር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ሲል የተቸው መግለጫው ይህ የማጠልሸት ዘመቻ “ድብቅ ሴራ ያዘለ እና የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚፃረር መሆኑን የትግራይ ህዝብ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እና የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በሚገባ ሊገነዘበው ይገባል” ሲል አሳስቧል።
“የሀሰት ክስ በመንዛት ህዝብን እና የዓለማቀፍ ህብረተሰብ በማደናገር ሌላ ድብቅ ፍላጎት ለመፈፀም መሞከር ፍፁም ሃላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው ሲል” አሳስቧል።
ህወሓት፣ የትግራይ ፀጥታ ሃይልም ሆነ የትግራይ ህዝብ፣ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር እነጂ ሌላ ድብቅ ፍላጎት የላቸውም ብሏል።
“በሰላማዊ ኣሰራር ተስፋ አንቆርጥም” ብለን ውስጣዊና ውጫዊ ሴራዎችን ተቋቁመን እየሰራን ባለንበት ሁኔታ፣ ዛሬም እንደ ትናንቱ ሁኔታውን ያልሆነ ምስል በማስያዝ ከሰላም ሂደቱ በተቃራኒ የሚኬድ እንቅስቃሴ በፍጥነት ሊታረም ይገባል” ሲል አሳስቧል።
“አሁንም ለሰላም ያለን መርህ ላይ የተመሰረተ አቋም በምንም መልኩ አይለወጥም” ሲል የገለጸው ህወሓት “ከሁሉም የጎረቤት ክልሎችና ሃገራት ህዝቦች ሰላማችንን ለማረጋገጥ እና አስተማማኝ ለማድረግ ጥረታችን ይቀጥላል” ብሏል። አስ