አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/ 2017 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ስር በሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች በጸጥታ ስጋት ምክንያት የመማር ማስተማር ሂደት መቋረጡን መምህራን እና የትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።
አቶ ንጉስ ተገኑ በቆቦ ከተማ በሚገኘው የካቶሊክ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ-መምህር ሲሆኑ እርሳቸው የሚሰሩበትን ትምህርት ቤት ጨምሮ በከተማዋ ያሉ በርካታ ትምህርት ቤቶች በአከባቢው ባለው ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት የተነሳ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ ማቆማቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
“ባለፈው ሳምንት አንድም ቀን አላስተማርንም። የመማር ማስተማር ሂደቱ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተቋርጧል። ፋንታው ድንቁ መታሰቢያ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ነበረ እስከዛሬ ሲያስተምር የነበረው እሱም ቢሆን በዛሬው ዕለት ዝግ ነው” ያሉት አቶ ንጉስ የመማር ማስተማር ሂደት መቋረጡ በአከባቢው ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ስጋት ጋር የተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል።
“አሁን ላይ ትምህርት የሚያስጀምር ሁኔታ የለም። መንግሥት እንድንጀምር ማስታወቂያ አስነግሯል። ከፋኖ በኩል ደግሞ የተወሰነ መቆየት አለበት ይላሉ” ብለዋል።
በተጨማሪም “በቆቦ ከተማ ዙርያ በሚገኙ ት/ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን የጥቅምት ወር ደመወዝ አልተከፈለንም በሚል ለሳምንት ያህል ማስተማር አቋርጠው የነበሩ ቢሆንም ውይይት ተደርጎ ከሶስት ቀናት በፊት ደመወዛቸው እንደተከፈላቸው ሰምቻለሁ” ሲሉ አክለዋል።
ሆኖም አሁን ላይ ቆቦ ከተማን ጨምሮ በዙርያዋ ባሉ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ እንደተቋረጠ ገልጸው ለዚህም “በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት የጸጥታ አካላት መካከል ባለው ግጭት የተነሳ እንጂ ከደመወዝ ጥያቄ ጋር በተያያዘ አይደለም።” ሲሉ አስታውቀዋል።
አያይዘውም አሁን ላይ በቆቦ ከተማ ስር የሚገኙና የመማር ማስተማር ሂደቱ ከተስተጓጎለባቸው በርካታ ትምህርት ቤቶች መካከል የቆቦ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ የእውቀት ጮራ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ የሚሊኒየም አንደኛ ደረጃ ት/ቤት እና አዲስ ዓለም (አልማ) ት/ቤት እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
ርዕሰ መምህር አክለው ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት በመንግሥት በኩል ትምህርት እንዲጀመር አቋም ተይዞ ተደጋጋሚ ውይይት ቢደረግም በአብዘሃኛው መምህር እና የተማሪ ወላጆች ዘንድ የዋስትና ጥያቄ መኖሩን ገልጸዋል።
ለአብነትም በራያ አከባቢ በሚገኝ አንድ ት/ቤት ላይ በቅርቡ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን ገልጸው ይህም በአከባቢው ያለውን የጸጥታ ስጋት እንዲጨምር ማድረጉን አስረድተዋል።
አዲስ ስታንዳርድ የድሮን ጥቃት ተፈፀመበት የተባለው ት/ቤት የ”ቀዩ ዳሪያ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት” መሆኑን እና ጥቃቱም ከአንድ ወር በፊት መፈጸሙን በዚሁ ትምህርት ቤት የቋንቋ መምህር ከነበሩ ግለሰብ ለመስማት ችሏል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት መምህሩ፤ በወቅቱ ትምህርት ቤቱ ተዘግቶ የነበረ በመሆኑ በድሮን ጥቃቱ የተጎዳ ሰው አለመኖሩን ተናግረዋል።
አክለውም በአከባቢው በሚንቀሳቀሱት በፋኖ ታጣቂዎች ተሰጥቷል ባሉት ማስጠንቀቂያ የተነሳ የመማር ማስተማር ሂደት መቆሙን ገልጸዋል።
“ትምህርት ለመጀመር አስቻይ ሁኔታ የለም። እኔ ስሰራበት በነበረው ት/ቤት መስከረም መጀመሪያ አከባቢ የተማሪዎች ምዝገባ ለማድረግ ሙከራ አድርገን ነበረ። የጸጥታ ስጋት በመኖሩ ምክንያት አልቻልንም።” ብለዋል።
ለአብነትም በራያ ቆቦ ወረዳ ዙርያ ከሚገኙ ት/ቤቶች መካከልም መንደፈራ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ጎላሽ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ዞብል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ራማ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ከመስከረም ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ ዝግ መሆናቸውንና ምንም አይነት የተማሪዎች ምዝገባ አለማከናወናቸውን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ከአምና 2016 ዓ.ም ጀምሮ ምንም አይነት የመማር ማስተማር ያላከናወኑ እንደ ምንዴና፣ ሐርበት እና ደርባ የተሰኙ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን አመላክተዋል።
መምህሩ “ትምህርት ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር ንክኪ የለውም። ትምህርት በመቋረጡም የሚጎዱት የራሳችን እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ናቸው። ስለሆነም መማር ማስተማሩ ቢቀጥል የተሻለ ነው።” ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።
በአማራ ክልል ባለው ግጭት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርት አለመጀመራቸው ይታወቃል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ በ2017 ዓ.ም. 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ቢያቅድም የተመዘገቡት ከ2 ሚሊዮን እንደማይበልጡ ገልጿል።
ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል በሰላም እጦት ችግር በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከሚገኙት 996 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተከፈቱት 86ቱ ብቻ መሆናቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።
በተመሳሳይ መልኩ በክልሉ ሰሜን ጎንደር ዞን ከሚገኙ 565 ትምህርት ቤቶች መካከል መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ የጀመሩት 192 ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ በቅርቡ አስታውቋል። አስ