ዋና ትረካፈጠራ

ትረካ፡ በወጣትነት እድሜው አመርቂ ስኬቶችን እያስመዘገበ ያለው የ22 ዓመቱ ሚሊየነር ኢዘዲን ካሚል

በብሩክ አለሙ@Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8/ 2016 ዓ.ም፡- የሰዎችን ህይወት በማቃለል ረገድ ፈጠራ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ በርካታ የፈጠራ ባለሙያዎች ካዩት ወይም ከገጠማቸው ችግር በመነሳት መፍትሄ የሚሆን ግኝትን በማበርከት የሰዎችን የእለት ተለት ህይወትን እያቃለሉ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት በርካታ ያልተቀረፉ ችግሮች በመኖራቸው እነዚህን ችግር ለመፍታት የሚረዱ ሀገር በቀል የፈጠራ ሥራዎች ጠቀሜታቸው የጎላ ነው፡፡

የፈጠራ ሥራዎች ወደ ምርት ገብተው ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉና ወደ ቢዝነስ እንዲቀየሩ ለማደረግ ሰፊ የሆነ የመንግስትና የባላሀብቶች ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ዘርፍ በእጅጉ ቢደገፍ ቀላል ሊባል የማይችል የውጭ ምንዛሬን የማስገኘት ትልቅ አቅም ያለው መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች ወደ ምርትና ገንዘብ እንዲቀየሩ በስፋት ሲሰራ አይስተዋልም ማለት ይቻላል፡፡

ምንም እንኳ ምቹ ሁኔታዎች ባይኖሩም ተፈናዎችን በማለፍ በፈጠራ ሥራቸው ስኬታማ መሆን ከቻሉት ባለሙያዎች አንዱ፣ ወጣት ኢዘዲን ካሚል ነው፡፡ “ችግር ፈቺ እንጂ ችግር ፈጣሪ ትውልድ አንሁን!” በሚል ንግግሩ የሚታወቀው የ22 ዓመቱ ኢዘዲን ካሚል የማህበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ በርካታ የፈጠራ እና የሶፍትዌር ሥራዎችን በመስራት በዚህ አጭር እድሜው ሚሊየነር መሆን የቻል ወጣት ነው፡፡

የፈጠራ ሥራ ባለሙያ እና የሶፍትዌር አበልፃጊው ኢዘዲን ተለወዶ ያደገው በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በዚያው ወልቂጤ ከተማ በሚገኘው ጉብሬ አብራ ፍራነሳ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ ኢዘዲን ገና ሰባትኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ነበር ወደ ፈጠራ ስራ እንዲገባ ምክንያት የሆነው ክስተት የተፈጠረው፡፡ ታዳጊው ኢዘዲን የእናቱ ዳቦ ቤት በሌቦች መዘረፉ ሌቦችን የሚቆጣጠር የፈጠራ ስራን እንዲሰራ አነሳሳው፡፡ ጊዜም ሳይወስድ ወዲያው በር ሲነካ ወደ አባቱ ስልክ ላይ ደውሎ የሚያሳውቅ የመጀመሪያ የፈጠራ ስራውን መስራት ቻለ፡፡

ኢዘዲን ወደ ፈጣራ ስራ ያስገባው አንደኛው ምክኒያት የእናቱ የንግድ ቤት መዘረፉ ይሁን እንጂ የቤተሰቦቹ የኑሮ ደረጃ ዝቅ ያለ በመሆኑ ራሱን እና ቤተሰቦቹን ለማገዝ ከአራተኛ ክፍል ጀምሮ ኢሌክትሮኒክስ እቃዎችን መጠገን መጀመሩ ለፈጠራ ባለሙያነቱ ትልቅ አስታዋፅዖ እንዳደረገለት ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል፡፡

ገና በልጅነቱ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን በመፈታታት መጠገን የተያያዘው ኢዘዲን ቤተሰቦቹ ትምህርቱ ላይ ተፅዕኖ ያደረስበታል በሚል አያደግፉትም ነበር፡፡ የቤተሰቦቹን ጫና በልጅ አዕምሮው ተቋቁሞ የቀጠለው ኢዘዲን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሽልማት ያስገኘለትን የፈጠራ ስራ ሲያበረክት ቤተሰቦቹ መሳሳታቸው ገብቷቸው ትምህርቱ ላይ ተፅዕኖ እንደማያደርግበት በማመን ልጃቸውን በመደገፍ ለአሁኑ ስኬታማው ኢዘዲን መሰረት መሆን ችለዋል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ገና በ14 ዓመቱ በሰራው የሌባ መቆጣጠሪያ ቴክሎኖጂ፣ ፈጠራን ሀ ብሎ የመጀረው ኢዘዲን ካሚል እስካሁን 37 የፈጠራ ስራዎችን እንካችሁ ማለት ችሏል፡፡ በፈጠራ ስራዎቹ በሀገር ውስጥ 14 ሽልማቶችን ውጭ ደግሞ ሁለት ሽልማቶችን መግኘት ያቻለው ይህ ወጣት ከሁሉም በ2011 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያበረከቱለት የብር ሜዳልያ ሽልማት ብዙ በሮችን የከፈተለት በመሆኑ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሽልማት መሆኑን ይናገራል፡፡ ቀጥሎም የጉራጌ ዞን መምህራን ማህበር ላበረከተለት ሽልማት ትልቅ ቦታ እንዳለውም ገልጧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኢዘዲን የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በተመባባር ያዘጋጀው ውድድር ላይ ለሁለት ተከታታይ አመታት አሸናፊ መሆን የቻለ ሲሆን፣ በጣና አዋርድ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍም ሁለት ግዜ ተሸላሚም ነው፡፡ ኬር ሽልማት ላይ ተስፋ የተጣለበት ወጣት ዘርፍ ተሸላሚ ነው፡፡ የአሜሪካ ኢምባሲ ባዘጋጀው የሶለቭት የፈጠራ ስራ ውድድር ላይ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡

ኢዘዲን ከሰራቸው የፈጠራ ስራዎች ውስጥ ኤክስ ዲሰተርብ የሚባለው አንዱ ሲሆን ይህ የፈጠራ ስራ በስብሰባ አዳራሽ፣ ቤተ-መፅሐፍት እና በመሳሰሉት ስፍራዎች ሰዎች ስልካቸውን ሳይለንት ማድረግ ሳይጠበቅባቸው ስላከቸውን ዝም ማሰኘት የሚችል የፈጠራ ውጤት ነው፡፡

ኢዘዲን ከሰራቸው የፈጠራ ሥራዎች በስልክ አምፑል እና የኤልክትሪክ ምድጃን ማብራትና ማጥፋት የሚችል ቴክሎኖጂ፣ እሳት አደጋ በሚነሳ ግዜ ለቤተሰባ አባላትና ለእሳት አዳጋ ጥሪ ማዕከል በመደወል የሚያሳውቅ፣ በስልክ በመቆጣጠር ብቻ ሻይ እና ቡና ማፍላት የሚችል ማሽን፣ በፀሃይ ብርሃን እና በቻርጅ የሚሰራ ባለሶስት እግር ተሸከርካሪ ቴክኖሎጂ ከፊሎቹ ናቸው፡፡

የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ሀርፍ ላይ ያሉት የፈጠራ ግኝቶቹ ከሰራቸው የፈጠራ ስራዎች ምርጥ የፈጠራ ስራዎች የሚላቸው መሆኑን የሚገልፀው ኢዘዲን በእነዚህ ስራዎች አለም አቀፍ ሽልማቶች እንደስገኙለት ለአዲስ ስታንዳርድ አስረድቷል፡፡

“ለማህበረሰቡ ይጠቅማል የምልው የፈጠራ ስራዬ በፀሃይ ብርሃን እና በቻርጅ የሚሰራ ባለሶስት እግር ተሸከርካሪ አንዱ ነው” ሲል የገለፀው የፈጣራ ባለሙያው በዚህ ስራው ብሪቲሽ ካውንስል ባዘጋጀው የካርቦን ልቀትን መቀነስ የሚችል ቴክኖሎጂ ውድድር ላይ 5ሺ ፓውንድ ማሸነፍ ችሏል፡፡ 

ኢዘዲን በህይወቱ ላይ ትልቅ ለውጥ እንዲያመጣ የረዳው ክስተት ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝቶ ወደ ቱርክዬ ማቅናቱ መሆኑን ይናገራል፡፡ ይህ የትምህርት እድሎ ለበርካት አመታት ሲሰራበት ከቆየው ሃርድ ዌር በተጨማሪ ወደ ሶፍርዌር ኢንጂነሪንግ እንዲገባ እድል ሰጥቶታል፡፡ በቱርክ ቆይታው የድረ-ገፅ እና የመተግበሪያ ትምህርት ኮርሶች የመማር እድል ያገኘው ኢዘዲን ከአራት ወራት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ “ሄክስ ላብስ” የሚባል ድርጅት አቋቁሞ የተማረውን ወደ ተግባር በመለወጥ በሶስት ወር ውስጥ ብቻ 1.2 ሚሊዮን ብር መስራት መቻሉን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጧል፡፡

በአሁኑ ወቅም በቱርክ የጀመረውን ትምህርቱን በኦላይን እየተከታተለ ያለው የፈጠራ ባለሙያው እና የሶፍትዌር አበልፃጊው በአሁኑ ወቅት በ“ሄክስ ላብስ” ድርጅት  ከ20 ሰዎች የስራ እድል በመፍጠር ለተለያዩ የመንግስትና የግል ድርጅቶች ድረ-ገፆችንና የመተግበሪያዎችን የማበልፀግ ሰራን እየሰራ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሰው ሀብት አስተዳደር፣ የፋይናንስ አስተዳደርን ጨምሮ የተለያዩ ሲሰተሞችን በመስራት ላይም ይገኛሉ፡፡

በሀገራችን የፈጠራ ስራዎች በስፋት ተመርተው ለህዝቡ የማይቀርቡበት ምክንያት

በርካታ የፈጠራ ስራች የማህበረሰቡን አኗኗር፣ ችግር የሚያቃልሉ በመሆኑ በስፋት ተመርተው ለህዝብ ቢቀርቡ ትልቅ ጥቅም ይሠጣሉ፤ ነገር ግን የፈጠራ ስራዎች ወደ መሬት ወርደው ሲተገበሩ አይታይም፡፡ ይህ ወጣት የፈጠራ ባለሙያ እና የሶፍትዌር አበልፃጊ የዚህ ዋነኛ ምክንያት ወደ ምርት ለመቀየር የሚያስፈልገው የገንዘብና የቦታ እጥረቶች መሆናቸውን ይናገራል፡፡ የሰራቸውን 37 የፈጠራ ስራዎች ወደ ምርት በመቀየር ለማህበረሰቡ ለማድረስ በማቀደ “አይከን አፍሪካ” የሚባል ድርጅት አቋቁሞ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ያስታወሰው ኢዘዲን የገንዘብ ድጋፍ አለመኖር የፈጠራ ባለሙያዎችን ስራቸውን ለህዝቡ እንዳያደርሱ ማድረጉን ይናገራል፡፡

“በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት ወደ ማድረጉ ገና እየተገባ በመሆኑ ባለሃብቶች መድፈር አይፈልጉም” የሚለው ኢዘዲን የፈጠራ ስራዎቹ ላይ ኢንስት እንዲያደርጉ ስምንት ባለሃብቶችን አነጋግሮ ፍቃደኛ አለሞሆናቸውን ጠቅሶ ገንዘብ ማጣት ለፈጠራ ባለሙያዎች ትልቅ ፈተና መሆኑን ገልጧል፡፡

“ይንን ለመቅረፍ በመንግስት የሚያሳየው ድጋፍ በቂ ባይሆንም ጥሩ የሚባል ጅማሮ ግን አለ” ያለው ኢዘዲን “ የዲጂታል ዘዴዎችን በማመቻቸት ረገድ ጥሩ ስራዎች እየተሰሩ ነው፤ በሃርድ ዌር ላይ ግን መንግስት በትኩረት መስራት ይጠበቅበታል” ብሏል፡፡

የፈጠራ ባለሙያዎች ጥሬ አቃዎችን ከውጭ ሲያስገቡ ከነጋዴ እኩል ቀረጥ የሚከፍሉ በመሆኑ ለባለሙያው አመቺ ሁኔታን አለመፍጠሩን አክሎ ገልጧል፡፡

ፈተናዎች

ከዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰብ ከመወለጁ አንፃር እንዲሁም የተወለደበት አካባቢ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ባለመኖራቸው በራሱ ፈተናዎች መሆናቸውን የሚናገረው ወጣቱ ትልቁ ፈተና ብሎ የሚያስበው ግን የፈጠራ ስራ ሲጀምር ወላጆቹ የማይጠቅም እየመሰላቸው እንዲተው የሚያሳድሩበት ተፅዕኖ መሆኑን ይናገራል፡፡ “ልጆች እንዳንዴ ሲደገፉ የመተው፤ ተው ሲባሉ ደግሞ አምቢ የማለት ዝንባሌ ያላቸው በመሆኑ ወላጆቼ ተው ባይሉኝ ኖሮ ምናልባት በፈጠራ ስራ ላልቀጥር እችል ነበር” ሲል የተናገረው የፈጠራ ለሙያው በወላጆቹ አለመደገፍ እንደ ጥሩ አጋጣሚ እንደሚወስደው ገልጧል፡፡

“ሌላኛው ትልቅ ፈተና የምለው የተፈራ ስራዎቼን ወደ ምርትና አገልግሎት ለመቀየር የገንዘብ ማጣት ነው” የሚለው ኢዘዲን ይህንን ፈተና የተለያዩ ሽልማቶች ላይ ተሳትፎ በማሸነፍ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ማለፍ መቻሉን ገልጧል፡፡ 

ቀጣይ እቅድ

ኢዘዲን ካሚል በቀጣይ የኦንላይን ግብይት ኢ-ኮሜርስ ላይ በሰፊው ለመስራት አቅዷል፡፡ እንደ ኢዘዲን ገለፃ ከሆነ ሰዎች የሚሸጡ እቃዎችን ፎቶ በማንሳት ኦንላይን ላይ በማሻሻጥ ገቢ ያሚያገኙበትን መድረክ በመገንባት ላይ ነው፡፡ በዚህም የኦንላይን ግብይት ለርካታ ስራ አጥ ሰዎች የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጧል፡፡  

የ22 አመቱ ወጣት ኢዘዲን በአሁን ወቅት ሚሊየነር መሆን መቻሉን እና 30 አመት ሳይሞላው ቢሊየነር የመሆን እቅድ እንዳለው ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጧል፡፡ “ፎርብስ መፅሔት ላይ ከ30 አመት በታች ቢሊየነር ዝርዝር ውስጥ መግባት ፈልጋለው” ሲል የገቢ እቅዱን የገለጸው ኢዘዲን በአሁኑ ወቅት ለተለያዩ ድርጅቶች እየሰሩ ባሉት የድረ-ገፅ እና የመተግበሪያ ስራ ጥሩ ገቢ እያገኙ እንደሆነ ገልጧል፡፡

ምክር ለወጣቶች

የፈጠራ ባለሙያ መሆን የሚፈልጉ ወጣቶች በቻሉት መጠን ሀሳባቸውን ወደ መሬት ለማውረድ መጣር ይጠበቅባቸዋል የሚለው ኢዘዲን የህን መድረግ የገንዘብ እጥረት ካለባቸው በሳምፕልም ቢሆን እንዲሰሩት ምክሩን ለግሷል፡፡ ጥሩ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ሰዎች የቻሉትን ያህል ኢንቨስት ሊያደርጉ የሚችሉ ሰዎችን ማነጋገር ይጠበቅበባቸዋል ብሏል፡፡ ኢዘዲን ለሱ ስኬት መንገድ የጠረገለት የተለያዩ ሽልማቶች ላይ ተወዳድሮ ገንዘብ ማሸነፍ መቻሉ መሆኑን ገልፆ ጀማሪ የፈጠራ ባለሙያዎች ሽልማቶች ላይ ተወዳድረው ካሸነፉ የሚያገኙት ገንዘብ ሀሳባቸውን ወደ መሬት ለማውረድ ትልቅ እድል የሚሰጣቸው ነው ብሏል፡፡ አስ

ተጨማሪ አሳይ
Back to top button